“ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” (ሉቃ.፩፥፵፰)

ስለ እመቤታችን ምሥጋና በአግባቡ ለመረዳት ቅዱሳት መጻሕፍት በሰከነ አእምሮ ከማጥናት እና ከማንበብ ባለፈ ድንግልን ለማመስገን የመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ መሠረት መሆኑ የታወቀ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው›› (ሮሜ፡፰፥፬) እንዳለው ያለ መንፈስ ቅዱስ መሪነት ማንኛውም ተግባር ማከናወን እና የተቃና እውነተኛ ሕይወት መምራት አይቻልም፡፡

በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሕይወትን መምራት የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን ምልክት ነው፡፡ ለእመቤታችን ምስጋና፣ ስግደት ስለ ማቅረብ ስለ አማላጅነቷ እንዲሁም ክብሯን ለመቀበል የሚታወኩትን ስንመለከት ከአእምሮ በላይ የሆነውን የመንፈስ ቅዱስ አሠራርን አለማስተዋላቸውንና የእግዚአብሔር ልጆች አለመሆናቸውን እንረዳለን፡፡ እመቤታችንን ለማመስገን የመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ረዳትነት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ያለ መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ቅድስት ድንግል ማርያምን ማመስገን አይቻልም፡፡

ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ‹‹የነቢያት ትንቢታቸው የሐዋርያት ዜናቸው አንቺ ነሽ› ያላትን እመቤታችንን አበው በሱባኤያቸው መልስ ያገኙባትን አለመቀበል  የአእምሮ ይቡስነት (ድንቁርና) ተጭኖታል ከማለት ውጭ ምን ማለት ይቻላል፡፡ (ውዳሴ ማርያም ዘማክሰኞ ፮)

ቅዱሳት መጻሕፍት በመተባበር የሚመሠክሩት እመቤታችንን ለማመስገን የመንፈስ ቅዱስ ረድኤት አስፈላጊ ስለ መሆኑ ነው፡፡ ለዚህም በአጭሩ ሁለት ምስክርነት ማለትም ከሰማያውያን ቅዱሳን ቅዱስ ገብርኤል እና ከምድራውያን የቅድስት ኤልሳቤጥ ምስክርነት እናያለን፡፡

ቅዱስ ገብርኤል የተላከው ከእግዚአብሔር ለመሆኑ እያንዳንዱ ያቀረበው ምስጋናና አክብሮት ምስክር ነው፡፡ ቃሉም የሚለው ‹‹ወበሳድስ ወርኀ ተፈነወ ገብርኤል መልእክ እምኀበ እግዚአብሔር፤ በስድስተኛው ወር ገብርኤል መልአክ ከእግዚአብሔር ተላከ›› ….የተላከው  ብርሃናዊ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ወደ እርሷ ገብቶ እየወደቀ እየተነሳ ክብርት ልዕልት ንጽህት መሆኗን እና ስለ ተሰጣት ጸጋ ተጠንቅቆ በቅደም ተከተል የተናገረው እንዲህ በማለት ነበር ‹‹ደስ ይበልሽ ጸጋ የሞላብሽ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ›› አላት፡፡ (ሉቃ. ፩፥፳፰-፳፱)

ሌላ ምስክርነት ደግሞ ቅድስት ኤልሳቤጥ ለእመቤታችን ያቀረበችው ምስጋና ነው፡፡ ስለ ድንግል ማርያም እና ስለ ልጇ ወዳጅዋ የመሰከረችው በመንፈስ ቅዱስ ተመርታ ነበር። ይህም ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ እንዲህ በማለት ምስክርነቱን ይሰጣል ‹‹ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ጽንሱ በማሕጸኗ ውስጥ  በደስታ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት››።  ድምጿን አሰምታ እንዲህ አለች ‹‹አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ  ነሽ፤ የማኅጸንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታየ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮየ በመጣ ጊዜ ጽንሱ በማኅጸኔ በደስታ ዘልዋልና››። ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈጸማል እና ያመነች ብጽዕት ናት። (ሉቃ.፩፥፵፩-፵፮)

የፅንሱ በማኅፀን መዝለል እና ማመስገን፣ የቅዱስ ገብርኤል የምስጋና አቀራረብና ምስክርነት እንዲሁም እመቤታችን እና የመልአኩ ቃለ ተዋስኦ  ምስጋናዋ ከእግዚአብሔር ስለ መሆኑ በቂ ማሳያ ነው፡፡ እመቤታችንም ‹‹ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል›› ማለትም ትውልደ ሴም፣  ትውልደ ያፌት  እና ትውልደ ካም ያመሰግኑኛል ብላለች። (ሉቃ.፩፥፵፰) ከእግዚአብሔር የተላከ ብርሃናዊ መልአክ ካመሰገናትና በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘች ቅድስት ኤልሳቤጥ ካወደሰቻት በማኅፀን ያለ ፅንስም በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ከሰገደ ዛሬም  እመቤታችንን ማመስገን የእግዚአብሔር ልጅ መሆንና ጸጋ መንፈስ ቅዱስ የመቀበል አንዱ ምልክት ነው፡፡ እመቤታችን አለማመስገን ከእግዚአብሔር ልጅነት መውጣት ነው፡፡ ምክንያቱም እርሱ እግዚአብሔር የተቀበላቸውን እና ያከበራቸውን አለመቀበል እንዲሁም አለማክበር የእግዚአብሔርን ፍቃድ አለመፈጸምና እግዚአብሔርን አለማክበር ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲህ ነበር ያለው ‹‹እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል›› (ማቴ. ፲፥፵)

ስለዚህም እመቤታችንን ማመን ማለት ክብሯን ንጽህናዋን፣ ቅድስናዋን እና ምስጋናዋን መቀበል ማለት ነው፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ የምናየው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል  የሚከተለው ይሆናል። በኦሪት ዘጸኣት እንደምንመለከው ‹‹በዚያን ቀን እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከግብጻውያን እጅ አዳናቸው ፤…እግዚአብሔር በእንዴት ያለ  ታላቅ ኃይል ግብጻውያንን እንዳሸነፈ እስራኤላውያን ባዩ ጊዜ  እግዚአብሔርን ፈሩ በእግዚአብሔር እና በሙሴ አመኑ›› አሁን እስራኤላያን በሙሴ እና በእግዚአብሔር አመኑ ተብሎ መጸፉ እስራኤላውያን ሙሴ እና እግዚአብሔርን አስተካክለው አመለኩ እንዲሁም ሙሴን እንደ እግዚአብሔር አዩት ማለት አይደለም። አስራኤላውያን በእግዚእብሔር ያመኑበት ማመን እና በሙሴ ያመኑበት ማመን የተለየ መሆኑ አስተዋይ ሰው ልብ ይለዋል። (ዘጸ. ፬፥፩ ፤ ዮሐ. ፭፥፮)

እመቤታችን ድንግል ማርያምን የምናመሰግናት ስለተሰጣት ጸጋ እና ክብር ነው። የተሰጣት ክብር ደግሞ ከጸጋ ባለቤት  ከልዑል እግዚአብሔር መሆኑን  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ  በመጽሐፈ ምሥጢር ላይ እንዲህ ይላል ‹‹ስለ ተሰጣትም የእግዚአብሔር ጸጋ የሔዋን መርገም በእርሷ ላይ ተቋረጠ  እንዲህ ያለ ስጦታ  ለአዳም እና ለዘሩ እስከ ዘለዓለም ለሌላ አልተሰጠም።›› በዚህ ብቻ ሳይሆን ስለ ንጽሕኗዋ፣ ስለ ቅድስናዋ ጭምር ምስጋና እናቀርባለን።

ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችንን ከመውደዱ የተነሳ እመቤቴ ምስጋናዋ እንደሰማይ ኮከብ እንደ ምድር አሸዋ በዝቶልኝ እንደ ልብስ ለብሼው እንደ ምግብ ተመግቤው ጠግቤ እያለ ሲመኝ ይኖር ነበረ። የሚሹትን መግለጽ ለእግዚአብሔር ልማዱ ነውና፤ ገልጾለት * ከአራት ሺህ በላይ ድርሰት ደርሷል። አኃዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ እስኪል ድረስ ። ሊቁ ያቀረበው ምስጋና መነሻው መንፈስ ቅዱስ እንደነበረ የሚከተለውን የአበው ትርጉም እንመልከት፡። “የነግህ ተግባሩን  አድርሶ ከመካነ ግብሩ ተቀምጦ ሳለ  እመቤታችን ትመጣለች የብርሃን ምንጣፍ ይነጠፋል፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል። በዚያም ላይ ሁና ሰላም ለከ ኦፍቁርየ  ኤፍሬም ትለዋለች፤ እርሱም ታጥቆ  እጆ ነሥቶ ይቆማል። ወድሰኒ ትለዋለች፤ እፎ እክል ወዶሶኪ ዘኢይክሉ ሰማያውያን ወምድራውያን። ምድራውያን ጻድቃን ሰማዕታት ሰማያውያን መላእክተ  አንቺን ማመስግን የማይቻላቸው ለእኔ እንደምን ይቻለኛል አላት። በከመ አለበወከ መንፈስ ቅዱስ ተናገር፤ መንፈስ ቅዱስ እንዳናገረህ ተናገር አለችው። በተረቱበት መርታት ልማድ ነውና …ከዚህም በኋላ ባርክኒ ይላታል፤ በረከተ ወልድየ ወአቡሁ መንፈስ ቅዱስ  ይኅድር በላዕሌከ ትልዋለች  ተባርኮ ምስጋናዋን ይጀመራል።

ስለ እመቤታችን ምስጋና እኛ ሊቁን ተከትለን “ብጽዕት አንቲ ኦ እግዝእትነ ማርያም ወላደተ አምላክ፤ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ ንዕድ ነሽ ክብር ነሽ። እስመ ብዓንኪ ዘአልቦ ትርጓሜ። ለምስጋናሽ ምሳሌ የለውምና። በማለት ክብሯን፣ በምስጋናዋን ከማግነን ሌላ ምን እንላልን። ሰው ሁኖ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚል እያለን የባሕርያችን መመኪያ ድንግል ማርያምን በማመስገን እና በመማጸን በርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ጸንተን ለመኖር ያብቃን፤ አሜን፡፡

ዲያቆን ልሳነጽድቅ ኪዳነ

ከማኅበረ ቅዱሳን ገጸ ድር

“በሕይወት መኖር የሚፈልግ ከክፉ ይሽሽ መልካሙንም ያድርግ”

በዚህ ወቅቱ ዓለም በከባድ እና አስቸጋሪ ፈተና ውስጥ ነው፡፡ ይህን ቸነፈር በሰው ጥንቃቄ ብቻ መቋቋም የሚቻል አይደለም፡፡ ሆኖም በግዴለሽነት እንዳንጓዝ ይልቁንም አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመክሩናል፡፡ በሃይማኖት ጸንተው በምግባር ቀንተው፣ ጥንቃቄም አድርገው የኖሩ አባቶቻችን በነፍሳቸውም፣ በሥጋቸውም ድነዋል፡፡ እኛም አባቶቻችንን አብነት አድርገን በነፍስም በሥጋም እንድንድን ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡

በሕይወት ለመኖር ከክፉ መራቅ መልካም የተባለውን ማድረግ  ያስፈልጋል፡፡ መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ “በምትገቡባትም በማንኛይቱም ከተማ ወይም መንደር በዚያ የሚገባው ማን እንደሆነ በጥንቃቄ መርምሩ” (ማቴ.፲፥፲፩) በማለት ያስተማረው አንዱ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን የነፍስም የሥጋም አምላክ ነው፡፡ የነፍሳችንንም ሆነ የሥጋችንን መጎዳት አይፈልግም፤ አይፈቅድምም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርን አምነን ከእኛ የሚጠበቀውንም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም በሚገቡበት ሀገርና ከተማ ሁሉንም ነገር በጥንቃቄ እንዲመረምሩ ታዘዋል፡፡ ለእነርሱ የተነገረው ትእዛዝ የእኛም ነውና የምንችለውን ጥንቃቄ ማድረግ ግድ ይላል፡፡

የዓለም ስጋት የሆነው የኮቪድ-፲፱ ኮሮና ቫይረስ ወደ አገራችን ገብቷል፡፡ ከሰዎች ጋር የምናደርገው ግንኙነት የተመጠነ፣ በቦታም የተራራቀ እንዲሆን ለተጎዱት መልካም ማድረግ  ይኖርብናል፡፡ በግዴለሽነት ከሚመጣብን መከራ እንድን፣ በሽታ ሊያስተላልፉ ከሚችሉ ነገሮች እንርቅ እንዲሁም ወረርሽኙ በእኛ ክፋት  ሊመጣ እንደሚችል በማሰብ በሽታውን ሊያባብሱ ከሚችሉድርጊቶች መራቅ ይገባል፡፡

የፈርዖንና ፈርዖናውያን ጭካኔያቸው ሲበረታና አልመለስ ሲሉ ከታዘዘባቸው መቅሰፍት አንዱ ቸነፈር ነው፡፡ እስራኤላውያንም እንዲሁ ከፈርዖናውያን ጭካኔ የሞላበትና የዐመፅ ግዛት ነጻ ያወጣቸውን አምላክ ረስተው በበደል ሕይወት ሲመላለሱ ያመጣባቸው መቅሰፍት ቸነፈር ነበር፡፡ ስለዚህ በዚህ ዘመን የመጣውንም መቅሰፍት በምን ምክንያት ይሆን ብሎ መገንዘብና ክፉ ከሆነው ነገር ሁሉ መራቅ ያስፈልጋል፡፡

መልካም ማድረግ፡- ምንም እንኳን በሽታው የሚተላለፍባቸው መንገዶች እርስ በእስር መተሳሰብን የሚያርቁ፣ መረዳዳትን የሚቃወሙ፣ አብሮነትን የሚጻረሩ ቢሆኑም ነገር ግን በባለሙያ ምክር እየታገዙ፣ ደግሞ ጽኑዕ የሆነውን የሃይማኖት ትምህርት ልብ እያሉ ቤተ ክርስቲያኗ የምታስተምረውን ቁርጠኝነት መወጣት የክርስትናችን መገለጫ መሆን አለበት፡፡

በእስራኤልም ታሪክ በሽተኞችን በአንድ በኩል ጤነኞችን በሌላ በኩል አድርጎ በሽታው እንዳይዛመት የማድረጉ ጥበብ እንደነበር መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ክሥተት በቅዱስ መጽሐፍ የተመዘገበው መማር ያለብንን ጥበብ እንድንማር ነው፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር ለሰዎች መፈተንና መውደቅ ምክንያት ከመሆን መቆጠብ እንዳለብን “መሰናክል ግድ ሳይመጣ አይቀርም  ነገር ግን መሰናክሉን ለሚያመጣው ወዮለት” (ሉቃ.፲፯፥፩) በማለት እንዳስተማረ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ከምንም በላይ የሚባሉ ጉዳዮችን ባለማስተዋል ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎችን ከወዲሁ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትታወቀው በእርስ በእስር መተሳሰብ፣ አብሮ በመብላት፣ አብሮ በመጠጣት፣ አንዱ ለአንዱ በችግሩ ወቅት በመድረስ ነው፡፡ በዘመናችን የመጣው መቅሰፍት ግን አብሮነትን፣ መተሳሰብን፣ አንዱ ለአንዱ መድረስን ወዘተ የሚያበረታታ አይደለም፡፡ ስለዚህ በበሽታው የተጠረጠሩትንም ሆነ መያዛቸው በእርግጠኝነት የተረጋጠባቸውን ሕመምተኞች የማግለል ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ምክንያት ሊከሠት የሚችለው አደጋ ደግሞ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሃይማኖታዊም ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ በበሽታው ምክንያት መገለል የደረሰባቸው ሰዎች በቀለኛ እንዲሆኑም ሊያስገድዳቸው ይችላል፡፡

በእርግጥ ኢትዮጵያ እንዲህ ያለውንም ዘመን አልፋበታለች፡፡ ምንም ዘመናዊ ግንዛቤ ባልነበረበት ወቅት እንዲህ ያለ ወረርሽኝ ሲመጣ ማታ ማታ በመሄድና በመጠየቅ፣ ከበሽተኛው ጋር ሊኖር የሚችለውን ንክኪ በመገደብ፣ በሽተኛው በምግብ እጦት፣ አይዞህ ባይ ባለመኖርና በብቸኝነት የባሰ ችግር ላይ እንዳይወድቅ ይጠይቁት ነበር፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነት እንደዚያ ያለውን ዘመን ካለፈች ዛሬ ደግሞ የተሻለ የባለሙያ ምክር ማግኘት የሚቻልበት፣ የትምህርቱም ሁኔታ አንጻራዊ በሆነ መንገድ የተስፋፋበት ዘመን ነውና ወቅቱ የሰጠንን የመከላከያ መንገድ ተጠቅመን ታሪክ ሊረሳው የማይችል ክፋት ሳይሆን ታሪክ ሊረሳው የማይቸል የመልካምነት ሥራ ልንሠራ ግድ ይለናል፡፡ ለዚህም ነው በሕይወት መኖር የሚፈልግ ከክፉ ይራቅ መልካሙንም ያድርግ የሚለውን መልእክት ማስተላለፍ የተፈለገው፡፡

አንዳንዴ ክርስትና የሚገለጸው በክፉና በአስጨናቂ ጊዜ መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “በእተዝ ይጼሊ ኀቤከ ኵሉ ጻድቅ በጊዜ ርቱዕ፤ ስለዚህ ጻድቅ ሁሉ በምቹ ጊዜ ወደ አንተ ይጸልያል።” (መዝ.፴፩፥፮) እንዳለን ምን አልባትም የእምነት ጽናታችን የሚፈተንበት ወቅት እንደሆነም መዘንጋት የለብንም፡፡ ምክንያቱም አንድ ጉዳይ በማድረግና ባለማድረግ የሚመጣውን ውጤት እንዲሁም የችግሩን ክብደትና ቅለት መለየት ካልተቻለ ብናደርገውም ባናደርገውም ጉዳት ይኖረዋል፡፡ ሶስና በረበናት እጅ ተይዛ ሳለ ያስጨነቃት በሁለቱም አቅጣጫ ጽኑዕ ሐሳብ ላይ የሚከት ጉዳይ ነበር፡፡ “ባደርገውም እሞታለሁ ባላደርገውም እሞታለሁ” (ዳን.፲፫፥፳፪) ያለችበት ወቅት ነበር፡፡ ታዲያ የሃይማኖት ጽናት በዚህ ጊዜ ይገለጻል፡፡ ነገር ግን የሚበልጠውን ጉዳት አስቀርቶ መጠነኛውን ጉዳት መሸከም ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ጊዜ በሽተኛውን መንከባከብ ነው የሚጎዳው ወይስ አለመንከባከብና በሽታው ወደ እኔ እንዳይዛመት ማደረግ ነው የተሻለው የሚለውን ማገናዘብና በጥንቃቄ መመልከት ግድ ይላል፡፡ ግን ይህን ያህልም ሊሆን ስለማይችል በባለሙያ ምክር በመታገዝ አስፈላጊውንና መልካም የሆነውን ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

የባለሙያ ምክርን ቸል አለማለት

 ጠቢቡ ሰሎሞን ይህን ሲያስረዳ “መልካም ምክር ትጠብቅሃለች፤ የተቀደሰች ማስተዋልም ትጋርድሃለች” (ምሳ.፪፥፲፩) በማለት ተናግሯል፡፡ የምክርን አስፈላጊነት በተመለከተ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም “ለሚያደርጋት ምክር መልካም ናት” (መዝ.፻፲፥፲) በማለት አስረድቷል፡፡ ታዲያ ለሚያደርጋት ተባለ እንጂ ሰምቶ ብቻ ለሚሄድ ምንም ፋይዳ እንደሌለው መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በሽታው እንዳይዛመት ከባለሙያ አንጻር የሚነገረውን መልእክት ሃይማኖትን በማይሸረሽር መልኩ መተግበር ይኖርብናል፡፡ ይህ ሲባል ግን እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ማድረግ ያለብንን የጸሎት፣ የጾም፣ የንስሓ ሕይወት ማጠናከርንም መዘንጋት የለብንም፡፡

ብዙዎቹ በባለሙያ የሚሰጡት መልእክቶች ከቤተ ክርስቲያን ሕግና ቀኖና አንጻር ተቀራራቢነት አላቸው፡፡ ለምሳሌ በሽታው እንዳይተላለፍ ከሚወሰዱ ጥንቃቄዎች መካከል ንጽሕናን መጠበቅ አንዱ ነው፡፡ ይህን ደግሞ ቤተ ክርስቲያንም አስፍታና አምልታ የምታስተምረው ነው፡፡ ማንም ክርስቲያን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባ ሰውነቱን ታጥቦ፣ ልብሱን አጥቦ፣ ንጹሕ ልብስ ለብሶ መግባት አለበት፡፡ የሌሎችን ሥነ ልቡና ከሚረብሹ የውስጣዊም ሆነ የውጫዊ ንጽሕናዎችን  መጠበቅ አለበት፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከምን ጊዜውም በበለጠ በዚህ ጊዜ ለምእመናን መድረስ አለባት፡፡ በትምህርቱ፣ የባለሙያን ምክር ተግባራዊ በማድረግ፣ በጸሎተ ምሕላው፣ ምእመናን ባለመገንዘብ ለምን የሚል ጥያቄ የሚያነሷቸውን ጉዳዮች ሕግና ሥራቱን በማሳወቅ፣ ማድረግ የሚገባቸውን አድርጉ ማድረግ የማይገባቸውን ደግሞ አታድርጉ በማለት ከመንግሥት በተሻለ መልኩ ቀዳሚ ሚና ልትወስድ ይገባታል፡፡ በዚህም በምእመናን ላይ የሚደርሰውን የሥነ ልቡና፣ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የሃይማኖታዊ ጫናዎችን መቀነስ ይቻላል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ቀኖና በሚፈቅደው መንገድ ሕመምተኞች አገልግሎት እንዳይሰጡ የሚደረግበትን መንገድ መፈለግ፡፡ ለምሳሌ እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ፈሳሽ ነገር ያለባቸው፣ ደም የፈሰሳቸውና የሚፈሳቸው፣ የሚጥል በሽታ ያለባቸው ወዘተ ምእመናን ቢሆኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን አይገቡም፤ ካህናትም ቢሆኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን አይገቡም አገልግሎትም አይሰጡም፡፡ ስለዚህ እንደነዚህ ያሉ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ Continue reading

የቤተ ክርስቲያን ፈተና በዘመናችን

ድብቅ ዓላማ ያላቸው ወገኖች ቤተ ክርስቲያንንና ክርስቲያኖችን ለማጥፋት ሰበብ በመፈለግ ጥፋተኛ እያስመሰሉ ያቀርባሉ፡፡ በመሠረቱ ይህ አስተሳሰብ ሁለት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡ የመጀመሪያው ታሪክ በመሰነድ፣ ትውልድ በምግባር ኮትኩታ ያቆየች ባለውለታ፣ ቅርሶቿ ለሀገር ልዩ መታወቂያ ጐብኝዎችን ማርኮ የሚያመጣ ሆኖ ሳለ ያለ ስሟ ስም መስጠቱ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከእውነት የራቀ ሐሳብ ይዘው ጥፋተኛ ሳትሆን፤ ጥፋተኛ ስለሆነችና ከአጥፊዎች ስለተባበረች መጥፋት ይገባታል እንበቀላት የሚለው ነው፡፡ እነዚህ ለማጥፋት ምክንያት ፈላጊ ወገኖች ቤተ ክርስቲያንን እያቃጠሉና ምእመናንን እየገደሉ ለምን ሲባሉ ጥፋተኛ ስለሆነች ይላሉ፡፡ መቼ፣ የት፣ በማን፣ እነማንን ተብለው ሲየጠቁ መልስ የላቸውም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ማቃጠልና ምእመናንን መግደል የእምነቱ ተከታዮች ራሳቸውን ወደ መከላከል ከዚያም ወደ መጉዳት ሊሸጋገሩ እንደሚችሉ መረዳት ይገባል፡፡ ለተፈጸመው ጥፋት አጸፋውን ቤተ ክርስቲያን ብትመልስ በሀገር ላይ ሊከሠት የሚችለውን ጥፋት አስቀድሞ መረዳትም ይጠቅማል፡፡ ጥናትን ሽፋን አድርጎ ለአጥፊዎች ዱላ የሚያቀብሉ አካላትም ከድርጊታቸው መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሥት አጥፊዎችን ለሕግ ከማቅረብ በተጨማሪ ለክርስቲያኖችና ለቤተ ክርስቲያን ከለላ መስጠት ይኖርበታል፡፡ አጥፊዎችም ክርስቲያኖችን ለማጥፋት የመዘዙት ሰይፍ ወደ ራሳቸው እንዳይዞር እና የእርስ በእርስ መጠፋፋት ሊያስከትል እንደሚችል ደጋግመው ሊያስቡበት ይገባል፡፡ በሃይማኖትና በዘር ምክንያት የተቀሰቀሰ ግጭት መብረጃ እንደሌለው በየሀገራቱ የተፈጸሙትን ጥፋቶች ማየት ይገባል፡፡ ታሪክ መጥቀስ ብቻውን የዕውቀት ባለቤት አያደርግም ከታሪክ መማር እንጂ፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰዎችን ለመንግሥተ ሰማያት ስታዘጋጅ፣ በፍቅር ስባ፣ በትምህርት አለዝባ በእምነትም በምግባርም እንዲስተካከሉ በማድረግ ነው፡፡ ከአፍሪካ ሀገራት መካከል ሀገራችን ብቸኛ የራሷ ፊደል ያላት፣ ዘመን ተሻግሮ ከዘመናችን የደረሰ ቅርስ አበርክታ ሀገራችን በመላው ዓለም እንድትታወቅ ያደረች ባለውለታ ናት፡፡ አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ ኢትዮጵያውያን የቅኝ ግዛት ቀንበርን ሰብረው ጥለው፣ የነጭን ትምክተኛነት አስተንፍሰው ልጆቻቸው ቀና ብለን እንድንሔድ የመሪነቱን ሚና የተጫወተች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በውጭ ሀገራት በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተጽፈው እምነት፣ ዕውቀት፣ ሥነ ምግባር የሚያስተምሩ መጻሕፍት ኢትዮጵያዊ በሆነ ብሂል ተተርጒመው ትውልድ እንዲማርባቸው፣ ሊቃውንቶቿ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በአውሮፓ የኢትዮጵያን ባህል፣ ሃይማኖት፣ ታሪክ በማስተዋወቅ የአምባሳደርነት ሚና እንዲጫወቱ ያደረገችው ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይህን የቤተ ክርስቲያን አስተዋጽኦ ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ “የኢትዮጵያ ምሁራን መነኮሳት በኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ክልል ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ውጭ በመሔድ በታሪክ ሊታወስና ሊጠና የሚገባ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ አካባቢ በሱዳንና በግብፅ፣ በየመንና በኢየሩሳሌም፣ በአውሮፓ በመሔድ እነሱም እየተማሩ፣ የውጭውንም ሕዝብ ስለ ኢትዮጵያ ቋንቋና ታሪክ፣ ሃይማኖትና ባህል እንዲያውቅና እንዲፅፍ አድርገዋል” (አክሊሉ፤፹፩) በማለት ገልጠውታል፡፡

እውነተኞቹ ተመራማሪዎች ያለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያን ማሰብ እንደሚከብድ በምርምራቸው አረጋግጠው እውነቱን ከሐሰት፣ ብስሉን ከጥሬ፣ የሚጠቅመውን ከሚጐዳው፣ የተፈጸመውን ካልተፈጸመው ለይተው ከጥንካሬያችን እንድንማር ከስሕተታችን እንድንጠበቅ ያደረጋሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ማዳከም ዓላማችንን ያሳካልናል ብለው የሚያስቡ ወገኖች ደግሞ ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ፈልገው ቅስማቸው ተሰብሮ እንዲመለስ ያደረገችው ቤተ ክርስቲያን መሆኗን ስለተረዱ ስሟን ለማጥፋት፣ ታሪኳን ለመበከል የጻፉትን አሉባልታ እውነት አድርገው በመውሰድ ታሪክ ሲያበላሹ፣ በተቀመጡበት የኃላፊነት ቦታ ጥፋት ሲፈጽሙ ይታያሉ፡፡ ሰውን በሰውነቱ እኩል ማገልገል ሲገባቸው በጎሳ፣ በቋንቋ፣ በጎጥ፣ በቡድንና በባህል በመከፋፈል ሥልጣንን ለክፉ ተግባር ይጠቀማሉ፡፡ ሕዝብን ለማገልገል የተሰጣቸውን ሥልጣን ተጠቅመው ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን የማሳደድ ተልእኮ ይፈጽማሉ፡፡ ሀገር ሰላም ካልሆነችና ዜጎቿ በሰላም ወጥተው ካለገቡ አጥፊዎችም ችግር እንደሚገጥማቸው አልተረዱትም፡፡

በካናዳ፣ በቫቲካን፣ በጀርመንና በሌሎችም ሀገሮች የኢትዮጵያ ጥናት ተቋማት እንዲከፈቱ፣ ተመርምሮ የማያልቅ ዕውቀት የያዙት የብራና መጻሕፍት ለዓለም እንዲተዋወቁ ያደረጉት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምራ “ሑሩ ወመሀሩ” ብላ ያሰማራቻቸው ሊቃውንት ናቸው፡፡ በሌላ በኩልም ሀገራችን እንግዳ ተቀባይ የሆነችውና ዓለም ፊቱን ያዞረባቸውን የመሐመድ ተከታዮች ሳይቀር መጠጊያ እንድትሆን ያደረጋት ቤተ ክርስቲያን በእምነት ኮትኩታ፣ በምግባር አንፃ ያስተማረቻቸው እነ ንጉሥ አርማህ ርኅሩኆች ብቻ ሳይሆኑ አስጠጉኝ ብሎ የመጣባቸውን አሳልፈው ለመስጠት ሰብአዊነት የተለያቸው ስላልነበሩ ጭምር ነው፡፡

“ወርቅ ላበደረ ጠጠር፣ እህል ላበደረ አፈር” እንዲሉ ይህን ውሉ ውለታ ለዋለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተሰጠው መልስ ነው፡፡ የደረሱበት መረጃ ካለ ማስረጃን መሠረት አድርጎ እውነት ማሳወቅ አንድ ነገር ነው፣ ሐሰትን እውነት እያስመሰሉ ማቅረብና ሰውን ለብጥብጥ መጋበዝ ግን ጤነኛ አእምሮ ያለው፣ በእግዚአብሔር የሚያምን ሰው የሚፈጽመው አይደለም፡፡ በየጊዜው ቤተ ክርስቲያንን የሚያቃጥሉት፣ ክርስቲያኖችን የሚገድሉት፣ ንብረታቸውን የሚቀሙትና የሚያሳድዱት ከመጥፎ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ መንግሥት እርምት ይወስዳል ቢባልም ምንም ነገር እንዳልተፈጸመ እየታለፈ፣ የማዘናጊያና የማረሳሻ ተግባር እየተፈጸመ ነው፡፡

ከምዕራባውያን የተኮረጀው ሥርዐተ ትምህርት ባልነበረበት ዘመን የሀገራቸው አምባሳደር የነበሩ፣ የውጭ ዲፕሎማት ሲመጣ አስተርጓሚ ሆነው ሲያገለግሉ የኖሩ ሊቃውንትን ያፈራችን ቤተ ክርስቲያን ከዋለችበት ላለማሳደር፣ ካደረችበት ላለማዋል እየተፈጸመ ያለው ግፍ መቆም አለበት፡፡ የሊቃውንቱን አስተዋጽኦ አክሊሉ ሀብቴ “ሆኖም እዚያ (ኢየሩሳሌም) የተደራጀው የመነኮሳት ማኅበር ኢትዮጵያን በመወከል ወደ ኢጣሊያም፣ ወደ አርመንም፣ ወደ ቊስጥንጥንያም፣ በመሔድ ግንኙነት ፈጥሮ እንደነበርና ምን አልባትም ከአርመኖች ጋር በነበረው የቅርብ ግንኙነት አርመኖች ፊደላቸውን ሊቀረፁ የቻሉት ከኢትዮጵያ ፊደል እንደሆነም ይነገራል፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም በሚመላለሱበት ዘመን እግረ መንገዳቸውንም ከሱዳንና ከግብፅ ክርስቲያኖች ጋር የቅርብ ግንኙነት መፍጠራቸው ይታመናል፡፡ የቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ምሁራን መነኮሳት ፈር ቀዳጅ አስተዋጽኦ እንዲሁ መጠናት የሚገባው ነው (አክሊሉ፣ ፷፪) በማለት ገልጠውታል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ ሰው አክባሪ፣ ሀገር ወዳድ፣ የሥራ ፍቅር ያላቸው፣ የራሳቸውን የማያስነኩ፣ የሌላውን የማይፈልጉ አድርጋ ስታሳድጋቸው ጠብ አጫሪነትን፣ በጉልበታቸው የሚመኩ መሆንን እንዲጸየፉ በማድረግ ነው፡፡ ጠላታቸውን በጽናትና በትዕግሥት እንዲቋቋሙ፣ ሀገርና ሃይማኖት ሊያጠፋ የመጣውን የጥፋት ኃይል እንዳያሸንፍ ያደረገች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይህ ድርጊቷ ያበሳጫቸው ምዕራባውያን በዘመናዊ ትምህርት ሰበብ በየሴሚናሪዎቻቸውና ኮሌጆቻቸው አስተምረው የላኳቸው ወገኖቻችን ነባሩን የኢትዮጵያ ሃይማኖትና፣ የክርስቲያኖች ተጋድሎ የሚያናንቅ፣ መልኩ የእኛ ቢሆንም የነጭ ጉዳይ አስፈጻሚ ሀገሪቱን ለባዕድ አሳልፎ ለመስጠት የባለቤትነት ስሜት የሚያድርበት እንዳይሆን አእምሮውን ለውጠው ሲልኩት ኖረዋል፡፡ በመመረቂያ ጽሑፍ ሰበብ ቤተ ክርስቲያንን ያለ ስሟ ስም፣ ያለ ግብሯ ግብር እየሰጡ የዘመናችን ተመራማሪ ነን ባዮች የግብር አባት ሆኑ፡፡ በዚህ ተግባራቸውም ትውልዱ በሰላም ውሎ እንዳይገባ እንቅልፍ ላጡ ወገኖች መንገድ መሪ የጥፋት ተባባሪ ሆነው አልፈዋል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ራሳቸውን ተሐድሶ ብለው የሠየሙ አካላት በተለያዩ የኅትመትና የብሮድካስት ሚዲያዎች በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያወርዱትን የስድብ ዶፍ መመልከት ይቻላል፡፡ በአካል መግዛት ያልተቻላቸውን ኢትዮጵያውያንን በአእምሮ ለመግዛት መሰሎቻችንንና በሥጋ የሚዛመዱንን አእምሮ እየለወጡ የሚልኩልንንና እነሱም አልፎ ሒያጅ መንገደኞችና ለቤተ ክርስቲያን ጥላቻ ያደረባቸውን ወገኖች እየጠየቁ የጻፉትን አሉባልታ በትክክለኛ ማስረጃ በመሞገት፣ የዕውቀታቸውን ግልብነት፣ የመረጃቸውን ተራነት፣ የትነታኔያቸውን አመክንዮ አልባነት ማሳየት ይኖርብናል፡፡ አጥፊዎች ታጥቀው ሲዘምቱብን ዝም ብሎ ማየት እሳት መቃጠሉን የሰማ የዋህ እኔስ ሣር ውስጥ ተደብቄያለሁ በማለት የመለሰውን የሚያስታውስ ይሆናል፡፡

Continue reading

ዝክረ ሰማዕታት “ዘኦሮሚያ”

ነገ ጥቅምት 16 ቀን 2012 ዓ.ም ÷ከጥዋቱ 3፡00 ጀምሮ÷አራት ኪሎ በሚገኘው÷ በመንበረ ጸባዖት ቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል÷ ከሰሞኑ በኦሮሚያ አንዳንድ አከባቢዎች በጽንፈኞ በተቀሰቀሰው ግጭትና ቅስቀሳውን ተከትሎ በደረሰባቸው ግድያ ÷ሰማዕትነት ለተቀበሉ ኦርቶዶክሳውያ በቅዱስ ሲኖዶስ የምልዓተ ጉባዔ አባላት እየተመራ÷የጸሎተ ፍትሐት መርሐ ግብር ይካሔዳል፡፡ በአዲስ አበባና ዙርያዋ የምትገኙ ኦርቶዶክሳውያን በሙሉ በዚህ መርሐ ግብር ላይ እንድትገኙ ጥሪ ተላልፏል፡፡ በስፍራው በሰዓቱ በመገኘት ለሰማዕታቱም ያለን አክብሮትና ለሰማዕታቱ ቤተሰቦች ያለንን አጋርነት እንግለጥ!! መርሐ ግብሩ ለሁሉም የሚዲያ አካላት ክፍት በመሆኑ መገኘት ትችላላቹ፡፡ Continue reading

ስቅለት

የነገሥታት ንጉሥ የሕይወት ራስ ኢየሱስ ክርስቶስን ጭፍሮች የእሾኽ አክሊል ጐንጒነው በራሱ ላይ ደፍተውለታል፤ የእሾኽ አክሊል በመቀዳጀቱ በዘፍ ፫፥፲፰ ላይ አዳምን አስቀድሞ “ምድር እሾኽንና አሜከላን ታበቅልብኻለች” ብሎት ነበርና ያነን መርገም ደምስሶለት ለአዳም ክሷል፡፡ ዳግመኛም አዳምና ሔዋን ምክረ ከይሲን ሰምተው የድል ነሺዎች አክሊል ተለይቷቸው ነበርና ያነን ሰማያዊ አክሊል እንደመለሰልን ለማጠየቅ፡፡ ይኽ ለካሳ አምላካችን ስለፈጸመው የድኅነት ምስጢር ቅዱሳት ደናግል በጥልቀት እንዲኽ አብራርተዋል፡-

“አስተቀጸልዎ ከመዝ ለርእሰ ሕይወት አክሊለ ሦክ …” (የሕይወት መገኛ ርሱን የእሾኽ አክሊልን አቀዳጁት፤ መላእክትን የብርሃን ራስ ቁር የሚያቀዳጃቸው የነገሥታት ገዢ የሚኾን ርሱን የሾኽ አክሊል አቀዳጁት፤ በሾኽ አክሊልም ከራሱ ክፍል ያቆሰሉት ሺሕ ናቸው፤ ከራሱም ቊስሎች ደም እንደ ውሃ በዝቶ ፈሰሰ፤ ፊቱም ደምን ለበሰ ሰውነቱም በደም ተጠመቀ፤ የጽዮን ልጆች እናቱ ያቀዳጀችውን አክሊል ተቀዳጅቶ አዩት፤ ተድላ ደስታ የሚያደርግበትና የሙሽርነቱ ቀን ነውና (መሓ ፫፥፲፩) … ነገር ግን የሾኽ አክሊልን በመቀዳጀቱ በምድራችን ላይ የበቀሉትን አሜከላና እሾኽ ርግማንን አጠፋልን (ዘፍ ፫፥፲፰)፤ ራሱንም በዘንግ በመመታቱ የታላቁን እባብ ሰባቱን ራሶቹን ዐሥሩን ቀንዶቹን አጠፋልን (ራእ ፲፫፥፩)) ብለዋል፡፡

ሊቁ ቅዱስ ኤራቅሊስም ስለፈጸመው ካሳ እንዲኽ አስተምሯል፡-

 “እንዘ ይትቄጸል አክሊለ ሦክ አብጠለ ኲነኔሁ ለቀኖተ ሞት ወእንዘ ቅንው ዲበ ዕፀ መስቀል ኢተዐርቀ እምነ መንበሩ…” (የእሾኽ አክሊል ደፍቶ የሞትን ሥልጣን ፍርድ አጠፋ፤ በመስቀል ላይ ተቸንክሮ ሳለ ከዙፋኑ አልተለየም፤ ከባሕርይ አባቱ ከአብ፤ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ አልተለየም፤ በምድር አይሁድ እንደ በደለኛ ሲዘብቱበት፤ መላእክት በሰማይ የከበረ ጌትነቱን ይናገሩ ነበር) (ቅዱስ ኤራቅሊስ)

እጆቹና እግሮቹ ስለመቸንከሩ አስቀድሞ በነቢዩ ዳዊት ዐድሮ በመዝ ፳፩፥፲፮ ላይ “ብዙ ውሾች ከብበውኛልና የክፋተኞች ጉባኤም ያዙኝ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ፤ ዐጥንቶቼ ኹሉ ተቈጠሩ እነርሱም አዩኝ ተመለከቱኝም” በማለት ውሻ ከአፉ ያወጣውን መልሶ ለምግብነት እንዲፈልገው፤ አይሁድም ኦሪትን እለፊ ካላት በኋላ ሲሠሯት በመገኘታቸው በውሻ መስሎ ትንቢት ያናገረባቸው ሲኾን፤ ይኽም ሊፈጸም ንጹሓት እጆቹና እግሮቹ በምስማር ከዕፀ መስቀሉ ጋር አያይዘው ቸንክረውታል፡፡

የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ሔዋን በእግሮቿ ወደ ዕፀ በለስን በማምራቷ በድላ ነበርና ለርሷ ካሳ ሊኾን ንጹሓን እግሮቹ ሲቸነከሩ፤ በእጆቿም በለስን በመቊረጧ ንጹሐ ባሕርይ አምላክ እጆቹ በችንካር ተቸንክረዋል፡፡ በመቸንከሩም ለ፭ሺሕ ፭፻ ዘመን በሰው ልጆች ላይ የሠለጠነ የሞት ችንካር ጠፍቶልናል፡፡

ምስጋና ይግባውና ኢየሱስ ክርስቶስ በመቸንከሩ ስለፈጸመው ካሳ ደናግል ሲተነትኑ፡-
“ወበቅንዋቲሁ ሠበረ ለነ ቀኖተ ሞት …” (በመቸንከሩም የሞት ችንካርን አጠፋልን፤ ሔዋን በእግሮቿ ወደ ዕፀ በለስ ስለ ተመላለሰች እጆቹንና እግሮቹን በመቸንከር ከፍሏልና፤ በእጆቿም የበለስን ፍሬ ስለቈረጠች ፈንታ በእውነት የእግዚአብሔር ቃል በሥጋው ከመስቀል ዕንጨት ጋራ ተቸነከረ) በማለት አስተምረዋል፡፡

መተርጒማን ሊቃውንት እንዳመሰጠሩት ጌታ በዕንጨት መስቀል ላይ መሰቀሉ ስለምን ነው ቢሉ?፤ እሾኽ በሾኽ ይነቀሳል ነገር በነገር ይወቀሳል እንዲሉ በዕፀ በለስ ምክንያት የገባውን ኀጢአት በዕፅ ለማውጣት በዕፀ መስቀል ላይ ተሰቅሏል፡፡

ጌታችን ከምድር ከፍ ከፍ ብሎ ስለምን ተሰቀለ?

“እምከመ ተለዐልኩ እምድር እስሕብ ኲሎ ኀቤየ” (ከምድር ከፍ ከፍ ባልኊ ጊዜ ኹሉን እስባለኊ) ብሎ ነበርና ይኽነን ሊፈጽም ነው (ዮሐ ፲፪፥፴፪)፡፡

ዳግመኛም ከምድር ከፍ ከሰማይ ዝቅ ብሎ መሰቀሉ “ኅሩይ ማእከለ እግዚአብሔር ወሰብእ” እንዲል አምላክ ወሰብእ ኾኖ እንዳስታረቀን ለማጠየቅ፡፡

በመጨረሻም ምድርን በኪደተ እግሩ እየተመላለሰ እንደ ቀደሳት፤ ዐየራትን ደግሞ ሥብ እያጤሱ አስተራኲሰውት ነበርና አየራትን ለመቀደስ ነው፡፡

ንጹሐ ባሕርይ ጌታችንን አይሁድ መስቀሉን አሸክመው ቀራንዮ ወደሚባል ቦታ ከወሰዱት በኋላ ኹለት ወንበዴዎችን በቀኝና በግራ አድርገው ጌታችንን በመኻከል ሰቅለውታል (ማቴ ፳፯፥፴፰፤ ማር ፲፭፥፳፯፤ ሉቃ ፳፪፥፴፫፤ ዮሐ ፲፱፥፲፰)፡፡

ክፉዎች አይሁድ ይኽነን ያደረጉበት ምክንያት በክፋት ነው፤ ይኸውም በቀኝ የሚመጡ ሰዎች በቀኝ የተሰቀለውን ወንበዴ አይተው “ይኽ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ወንበዴ ነው” ይሏቸዋል፤ ከዚያም ጌታን “ይኽስ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ይኽስ ከርሱ ልዩ ነውን አንድ ነው እንጂ” ብለው ሰዎችን ለማሳሳት፤ በግራ የሚመጡ ሰዎች በግራ የተሰቀለውን ወንበዴ አይተው “ይኽ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ወንበዴ ነው” ይሏቸዋል፤ ከዚያም ጌታን “ይኽስ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ይኽስ ከርሱ ልዩ ነውን አንድ ነው እንጂ” ብለው ሰዎችን ለማሳሳት ያደረጉት ነው፡፡
ዳግመኛም አነገሥንኽ ብለውታልና ቀኛዝማች ግራዝማች ሾምንልኽ ለማለት ለመዘበት፡-
በተጨማሪም ነቢዩ ኢሳይያስ በምዕ ፶፫፥፲፪ ላይ “ከዐመፀኞችም ጋር ተቈጥሯልና” የሚለው ትንቢቱን ሊፈጽም ሲኾን ምስጢሩ ግን እኛን ከጻድቃን ጋራ አንድ ያደርገን ዘንድ ርሱ ከበደለኞች ጋር ተቈጥሯል፤ ሌላውም በዕለተ ምጽአት እኛን ኃጥኣንን በግራ ጻድቃንን በቀኝ ታቆማለኽ ሲያሰኛቸው ነበር (ማቴ ፳፭፥፴፫፤ ራእ ፩፥፯)፡፡

በኹለት ወንበዴዎች መኻከል ከሰቀሉት በኋላ ጲላጦስም “የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚል ጽሕፈት በዕብራይስጥና በሮማይስጥ በግሪክም ጽፎ በመስቀሉ ላይ አኖረው፤ (ዮሐ ፲፱፥፲፰-፳፪)፤ የአይሁድ ካህናት አለቆች ጲላጦስን “ርሱ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ እንዳለ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለኽ አትጻፍ” ሲሉት፤ ጲላጦስም “የጻፍኹትን ጽፌአለኊ” ብሎ መልሶላቸዋል፤ ይኽነንም በሕማማት ድርሳኑ ላይ ሲተረጒሙት፡- “ወዝ መጽሐፈ ጌጋይ ዘጸሐፎ ጲላጦስ ወአንበሮ መልዕልተ ርእሱ ይደምስስ ለነ በኲሉ ጊዜ መጽሐፈ ዕዳነ ዘጸሐፉ አጋንንት” (ጲላጦስ ጽፎ ከራሱ በላይ ያኖረው በደሉን የሚናገር ይኽ መጽሐፍ ኹልጊዜ አጋንንት የጻፉትን የዕዳችንን መጽሐፍ ያጠፋልን ዘንድ ነው) በማለት አራቅቀው ገልጠዋል፡፡

ጌታችን በሚሰቀልበት ጊዜ ብርሃን ያለበሳቸውን አምላክ ዕርቃኑን ለመሰወር ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ፀሓይና ጨረቃ ብርሃናቸውን ነሥተዋል (ማቴ ፳፯፥፵፭፤ ማር ፲፭፥፴፫፤ ሉቃ ፳፫፥፵፬-፵፭)፡፡ ይኽ በጌታ ስቅለት ዕለት እንደሚደረግ አስቀድሞ በነቢዩ አሞጽ ኹለት ጊዜ በትንቢት ተነግሯል፡- ይኸውም
“የእግዚአብሔር ቀን ብርሃን ሳይኾን ጨለማ አይደለምን? ጸዳል የሌለውም ድቅድቅ ጨለማ አይደለምን?” (አሞ ፭፥፳)

በዚያም ቀን ፀሐይ በቀትር እንድትገባ አደርጋለኊ ይላል ጌታ እግዚአብሔር በብርሃንም ቀን ምድሩን አጨልማለኊ” (አሞ ፰፥፱) ተብሎ

በዕለተ ዐርብ በጌታችን ስቅለት ዕለት ስለተደረገው ስለዚኽ ታላቅ ተአምር ሊቃውንት እንዲኽ ይገልጹታል፡-

“ጐየ ፀሓይ ወጸልመ ወርኅ ወከዋክብትኒ ተኀብኡ ከመ ኢያብርሁ ለምእመናን በጊዜ ስቅለቱ ቅዱስ እንዘ ፍጹም በገሃሁ ወርኅ ኢያብርሀ…” (ፀሓይ ብርሃኑን ነሣ ጨረቃም ጨለመ፤ ከዋክብትም በከበረ ስቅለቱ ጊዜ ለምእመናን እንዳያበሩ ብርሃናቸውን ነሡ፤ ጨረቃም በምልአቱ ሳለ አላበራም፤ ፀሓይ ብርሃኑን በነሣ ጊዜ ፍጡራን ኹሉ በጨለማ ተያዙ፤ የፈጠራቸው ፈጣሪያቸው እንደ ሌባ እንደ ወንበዴ በዕንጨት ላይ ተሰቅሎ እንዳያዩ ቀኑ ጨለመ፤ ባለሟሉ መልአክም ከሓድያንን ያጠፋቸው ዘንድ ሰይፉን በእጁ መዝዞ ይዞ ከመላእክት መኻከል ወጣ፤ የክርስቶስም ቸርነት በከለከለችው ጊዜ ያ መልአክ የቤተ መቅደሱን መጋረጃ በሰይፉ መታው ቀደደውም፤ ከላይ እስከ ታችም ወደ ኹለት አደረገው (ማቴ ፳፯፥፶፩፤ ማር ፲፭፥፴፰፤ ሉቃ ፳፫፥፵፭)፤ መላእክትም ኹሉ በሰማይ ኹነው ርሱን አይተው በአንድነት ሲቈጡ የአብ ምሕረቱ፣ የወልድ ትዕግሥቱ፣ የመንፈስ ቅዱስ ቸርነቱ ከለከለቻቸው፤ ፀሓይ ብርሃኑን ነሣ፤ በጨለማ ተይዞ ሲድበሰበስ ዓለምንም ተወው፤ ይኽ ኹሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ከሥጋው ከመለየቱ አስቀድሞ ተደረገ) (ቅዱስ አትናቴዎስ)
“እስመ ሶበ ተሰቅለ ክርስቶስ ጸልመ ሰማይ አሜሃ ወፀሓይኒ ሰወረ ብርሃኖ ወወርኅኒ ደመ ኮነ…” (ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ ያን ጊዜ ሰማይ ጨለማ ኾነ፤ ፀሓይም ብርሃኑን ነሣ፤ ጨረቃም ደም ኾነ፤ ምድርም ተነዋወጠች ደንጊያውም ተከፈለ፤ መቃብራትም ተከፈቱ፤ ስለዚኽም ለፍጡራን ከፈጣሪያቸው ጋር ሊታመሙ ተገባቸው (ማቴ ፳፯፥፵፭-፶፩) (ቅዱስ ሱኑትዩ)

“ፀሓይ ጸልመ ወወርኅ ደመ ኮነ ወከዋክብት ወድቁ ፍጡነ ከመ ኢይርአዩ ዕርቃኖ ለዘአልበሶሙ ብርሃነ” (ፀሓይ ጨለመ፤ ጨረቃም ደም ኾነ፤ ከዋክብትም ፈጥነው ወደቁ፤ ብርሃንን ያጐናጸፋቸውን የጌታን ዕርቃን እንዳያሳዩ) (አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ)
ሊቁ አባ ጊዮርጊስም ምስጢሩን በመጠቅለል በሕማማት ሰላምታው ላይም፡- Continue reading

“እንኳን ወጡ!” ወይስ “ለምን ወጡ!” እንበል?

በቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ

የሰሞኑ ወግ የእህታችን የዘርፌ ከበደ በግልጽ ወደ ፕሮቴስታንቱ ዓለም መቀላቀል መሆኑን ሁላችንም ያየነው ጉዳይ ነው። በዚህ መነሻ የተለያዩ ሐሳቦች ሲሰነዘሩ እንመለከታለን። አንደኛው “ውስጥ ሆና ከምታሳስት መሔዷ ጥሩ ነው” ሲል ሌላው ደግሞ “መጀመሪያውኑም ከእኛ አልነበረችም ስለዚህ መውጣቷ አይደንቅም” ባይ ነው። ልጅቱ ተገፍታ እና ተገፍትራ እንደወጣች በማመን “ይኸው ወጣችላችሁ” የሚሉ አስተያየቶችም ተመልክተናል። ከኦርቶዶክሱ ውጪ ባሉት አስተያየት ሰጪዎች ዘንድ ደግሞ የድል አድራጊነት ስሜት እና አጋጣሚውን በመጠቀም ሌሎችንም ለመቀስቀሻነት የመጠቀሙ የተለመደ ዘዴ ቀጥሏል።

በመጀመሪያ ደረጃ ግን ስለዚህች እህት መነጋር ያስፈልጋል ወይ? 

መልሴ አዎ ያስፈልጋል የሚል ነው። ለምን እንደሚያስፈልግ ላብራራ። ዘርፌ ከምን ዓይነት ሕይወት እንደመጣች በአንደበቷ የተናገረችውን አድምጠናል። የነበረችበት ሕይወት በጎ እንዳልነበረ ራሷ የነገረችንንን መነሻ አድርገን ከተመለከትነው ከዓለማዊ ሕይወት መንፈሳዊ ሕይወት መምረጧ ሊያስመሰግናት ይገባል። ነገር ግን የመረጠችውን ኦርቶዶክሳዊ ሕይወት እንድታውቀው እና እንድትረዳው፣ ምንነቱንና ጣዕሙን ቀምሳ እንድታውቀው በማድረግ በኩል ትልቅ ችግር መኖሩን ገና ቀደም ብሎ ማየት ተችሎ ነበር። የሥራ ለውጥ እንጂ የሕይወት ለውጥ እንድታደርግ የመከራት፣ ያስተማራትና የመራት መምህር እና አባት ያገኘች አትመስልም። ይልቁንም ገና ከዘፈን መድረክ ከመምጣቷ ተዘጋጅቶ የቀረበላት ኦርቶዶክሳዊው መድረክ በርግጥም በኦርቶዶክስ መምህራን የተያዘ ባለመሆኑ መንፈሳዊ ድቀት እንዲገጥማት ያደረገ ይመስላል። በወቅቱ አጅበዋት ጀብ ጀብ ሲሉ ከነበሩት ብዙዎቹ በግልጽ ኦርቶዶክሳዊነታቸውን ጥለው መውጣታቸውን አይተናል።

እውነቱን ለመናገር ኦርቶዶክሳዊውን ሃይማኖተኝነት ሳታውቀው ለመታረድ እንደሚነዳ እንስሳ ዓይነ ኅሊናዋን ሸብበው የመሯት ሰዎች መጠቀሚያ እንደሆነች ይሰማኛል። ከዓለማዊው መድረክ ባልተለየ በረከሰ የሥጋ ፈቃድ ሊያጠምዷት በሚፈልጉ ጨካኞች የታረደች አቅም አልባ በግ አድርጌ እቆጥራታለኹ። የቤተ ክርስቲያናችንን ዐውደ ምሕረት እየተጠቀመች ነገር ግን የሃይማኖቷን ትምህርት ሳትማር በውስጥ ለውስጥ የኑፋቄ ትምህርት በመስጠት ለዛሬው ትልቅ ድራማና ትዕይንት ሲያዘጋጇት ለነበሩት ሰዎች ዓላማ ማስፈጸሚያነት የዋለች አንዲት ከርታታ ነፍስ ናት። ለመሆኑ እንዲህ ያለውን ኑፋቄ ሲያስተምሯት የነበሩት ሰዎች አሁን የት ናቸው? እርሷን ወደ ውጪ ልከው አብረዋት ሄዱ ወይስ አሁንም ቁጭ ብለው ሌሎች ዘርፌዎችን እያዘጋጁ ነው? ልብ ያለው ልብ ይበል።

ለምን ወጡ ማለቱ አይሻልም?

ሰዎች ጤናማ ሃይማኖት ከሌላቸው ምን መደረግ እንዳለበት ቅዱስ መጽሐፍ በትክክል ነግሮናል። የተመረዘ የሰውነት አካል አልድን ሲል እንደሚቆረጠው ሁሉ የሃይማኖት መመረዝ ያጋጠመው ሰው የማይድን ሆኖ ሲገኝ በውግዘት ይለያል። ሰዎች ከሃይማኖት መርከብ ላይ የሚወድቁት በተለያየ ምክንያት ነው። ጌታችን በወንጌል ያስተማረንን ምሳሌ ማንሣቱ ለዚህ የበለጠ ገላጭ ይሆናል። በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 15 ላይ ሦስቱ የመጥፋት ታሪኮችን አስተምሮናል። ከቁጥር 3-7 ላይ ከዘጠና ዘጠኙ በጎች አንዱ ስለጠፋበት ሰው ታሪክ ይናገራል። ከቁጥር 8-10 ደግሞ አሥር ድሪም ያላትና አንዱ የጠፋባትን ሴት ታሪክ ይነገርናል። ከቁጥር 11-32 ደግሞ «የጠፋው ልጅ» ታሪክ ተጠቅሷል።

1.የጠፋው በግ ለምን ጠፋ? በእረኞች አያያዝ ጉድለት፤

2.ሴቱቱ ድሪሟ (የወርቅ ጌጧ) ለምን ጠፋባት? በትክክል ስላላስቀመጠችው፤ በጥፋቷ፤

3.የጠፋው ልጅ ለምን ጠፋ? በማንም ጥፋት ሳይሆን ይሻለኛል፣ ይበጀኛል ብሎ አልሞ፣ አውጥቶና አውርዶ በራሱ ምክንያት ነው የጠፋው፤

በነዚህ ሦስት የጥፋት ታሪኮች ውስጥ ያለው የመጥፋት ውጤት ተመሳሳይ ቢሆንም ምክንያታቸው ግን እጅጉን የተለያየ ነው። የጠፋው በግ በአውሬ ቢበላም ጥፋቱ ግን ከመጀመሪያ የእርሱ አልነበረም። የወርቅ ጌጡም ቆሻሻ ላይ ቢወድቅ ወይም በሌላ ቢሰረቅም ጥፋቱ ግን የእርሱ አልነበረም። ነገር ግን በእነርሱ ምክንያት ባለመሆኑ ከመጥፋት አልዳኑም። የጠፋው ልጅ አጠፋፍ ግን ይለያል።

የዘርፌ አጠፋፍ ከላይ ካየናቸው የበጉን ወይም የድሪሙን አጠፋፍ የሚመስል ይመስለኛል። ከዘፈን መድረክ ወደ ዘፈን መድረክ ሲያቅበዘብዟት የኖሩት ሰዎች ግን ብዙ ዕዳ አለባቸው። “በሕይወቴ እረፍት አልነበረኝም” ስትል የነፍሷን መቅበዝበዝ የተናገረችው ትክክል ይመስለኛል። የሚያሳዝነው ግን ወደ ሌላ የጥፋት መንገድ በመግባት ዕድሜ ለንስሐ የማግኘት ተስፋዋን ማጨለሟ ነው። ይማርሽ እንበላት።

“ተመሳሳይ ላባ ያላቸው ወፎች በአንድ ላይ ይበራሉ”

================================
ኢዩ ጩፋ “እግዚአብሔር ያድናል” ብሎ ከልቡ ስለማያምን ፌደራል ፖሊስን አምኖ በእነሱ ይታጀባል ። ዘርፌ ደግሞ ኢዩ ጩፋን አምና ተቀብላዋለች ። እነሆ አብረው ይበሩማል ።

 

ቅዱስ ዑራኤል መልአከ ሰላም

ዑራኤል የሚለው ስም “ዑር” እና “ኤል” ከሚሉ ሁለት ቃላት የተመሠረተ ነው። ዑራኤል ማለት ትርጉሙ “የብርሃን ጌታ”፣ ”የአምላክ ብርሃን” ማለት ነው። ቅዱስ ዑራኤል ከ7ቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን ከፍጥረተ ዓለም ጀምሮ በመብረቅና በነጎድጓድ ላይ የተሾመ መልአክ ነው። በመሆኑም መባርቅት ለጥጋብና ለበረከት እንዲበርቁ ነጎድጓድም ለሰላም እንዲሆን
ያሰማራል። መ.ሄኖክ 6፥2 ምስጢረ ሰማይና እውቀትንም ሁሉ ለሄኖክ የገለጸለት የፀሐይን
የጨረቃን የከዋክብትንና የሰማይ ሰራዊትን ብርሃንን የሚመራ እርሱ መሆኑን ለሄኖክ ነግሮታል።

መ.ሄኖክ 28፥13 “ቅድስት ድንግል ማርያምን፣ ከልጇ ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወደ ግብጽ ስትሰደድ መንገድ የመራ፤ ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ በተሰቀለ ጊዜ፣ ክቡር ደሙን በብርሃን ጽዋ ተቀብሎ፣ በብርሃነ መነሳንስ በዓለም ላይ የረጨ፤ እውቀት ለተሰዎረባቸው ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል ጽዋ ጥበብን ያጠጣ፤ ኢትዮጵያዊውን ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መርካታ ቅዱሳት መጻሕፍትን አንዲደርሱ ያገዘ፣ የረዳና የዕውቀት ጽዋን ያጠጣ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ Continue reading

“ልጄን ከግብፅ ጠራሁት” /ት.ሆሴዕ 11፥1/

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስተዋሕዶ  ቤተክርስቲያን  ሕግናሥርዐት  ከመስከረም26 ቀን  እስከ ኅዳር 6 ቀን ያለው 40 ቀን  የእመቤታችንንእና የልጇን ስደት በማሰብወርኃ ጽጌን (ዘመነ ጽጌን) ታከብራለች፡፡ይህ 40ው ቀንየእመቤታችንና የጌታችን ስደትየሚታሰብበት ዘመን ነው፡፡ወቅቱ የአበባና የፍሬ ወቅትበመሆኑ እመቤታችን በአበባጌታችን በፍሬ እየተመሰሉጌታችን በአምልኮት እመቤታችን በፈጣሪ እናትነቷ በተለየ ምስጋና ይመሰገናሉ፡፡

 በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ አምሥቱን ጸዋትወ ዜማ ሲደርስ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳው አባ ጊዮርጊስ ደግሞ ሰዓታትን ደርሷል፡፡ በዚሁ ዘመን ከአባ ጊዮርጊስ ጋር ጥልቅ መንፈሳዊ ፍቅር የነበረው አባ ጽጌ ድንግል  ማኅሌተ ጽጌ የተባለውን ድርሰት ደርሷል፡፡  ማኅሌተ ጽጌ ግጥማዊ አካሄድ ያለው ድንቅ ኢትዮጵያዊ ድርሰትሲሆን ይህ ድርሰት በማንኛውም ጊዜ የሚጸለይ ቢሆንም በተለየ ሁኔታ ወቅት ተለይቶለት በቤተክርስቲያን አገልግሎት ላይ የሚውለው ግን   በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና በልጇየስደት ዘመን  ማለትም  ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ቀን ድረስ ባለው  ዘመን ውስጥ ነው፡፡

በዚህ ወቅት በየሳምንቱ እሑድ ሌሊቱን በሙሉ የእመቤታችንን ከልጇ ጋር ወደ  ምድረ ግብፅመሰደድና መንከራተት እየታሰበ በሊቃውንቱ  የሚደርስ የምሥጋና ጸሎትም  ነው ፡፡ ይህ ድርሰትበግጥም መልክ የተደረሰ  ሲሆን በአብዛኛው አምስት ስንኞች ሲኖሩት ብዛቱም 158 ያክል ነው፡፡እመቤታችን ጣዕሟንና ፍቅሯን እንዲሁም ምስጋናዋን ሲናፍቁ የነበሩትን ቅዱስ ኤፍሬምንና አባሕርያቆስን ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን እንደገለጸችላቸው  ሁሉ ለፍቅሯ ሲሳሳ ለነበረው ለአባ ጽጌድንግል ደግሞ ይህንን የማኅሌተ ጽጌን ድርሰት  እንዲደርስ ምስጢርን ገልጻለታልች ።

 በቅድስት ሐገር ሐገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ  የመስከረምና የጥቅምት ወራት የአበባ ወራትወርኅ ጽጌ (ዘመነ ጽጌ) ናቸው፡፡ ይህም ወቅት ተራሮች በአበባ የሚያጌጡበትና ለዓይን ማራኪየሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህም ዘመን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ልብስ ስለምን ትጨነቃላችሁ ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፡አይደክሙም፣ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደአንዱ አልለበሰም፡፡ እግዚአብሔር፣ ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣርእንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፣ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፣ እናንተንማ ይልቁን እንዴት፡፡ እንግዲህምን እንበላለን፣ ምንስ እንጠጣለን፣ ምንስ እንለብሳለን ብላችሁ አትጨነቁ (ማቴ 5÷28-33) በማለት የተናገረውን ቃል በማሰብ መጨነቅ የሚገባን መንግሥተ ሰማያት ለመግባት እንጂ በዚህዓለም ስላለው ነገር እንዳልሆነ ተራሮችን በአበባ ያለበሰ አምላክ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረንንእኛን ለኑሮ የሚያስፈልገንን ምግብና ልብስ እንደማይነሳን እያሰብን የምንዘክርበት ወቅት ነው፡፡

የሊቁ  ድርሰትም ፍሬ ከአበባ÷ አበባም ከፍሬ እንደሚገኘ ሁሉ ማኅሌተ ጽጌም እመቤታችንቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇን መድኃኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአበባና በፍሬእየመሰለ የሚያስረዳ ድርሰት ነው፡፡ እርሷን በአበባ ሲመስል ልጇን በፍሬ እርሷን በፍሬ ሲመስል ልጇን ደግሞ በአበባ እየመሰለ ይናገራል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ፣ወየዓርግ ጽጌ እም ጕንዱ  ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፤ ከሥሩም ቁጥቋጦ ያፈራል (ኢሳ . 11÷1) ብሎ ከእሴይ ዘር የምትገኘውን እመቤታችንን በበትር ፣ ከርሷ የሚገኘውን ክርስቶስንደግሞ በጽጌ መስሎ ትንቢቱን ተናግሯል፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም ድርሰቱን በዚሁ አንጻር በመቀመርእያንዳንዱን መልክዕ እመቤታችንንና ልጇን አስተባብሮ በጽጌና በፍሬ በመመሰል፣ ከዚያውበማያያዝ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ በምሥጢር፣ በታሪክ፣ በጸሎትና በመሳሰለው መልክ ድንቅበሆነና በተዋበ ሁኔታ አዋሕዶ ደርሶታል፡፡

ሊቁ አባ ጽጌ ድንግል በማኅሌተ ጽጌ ድርሰቱ እመቤታችንን በአበባ እየመሰለ ከተናገረው   ድርሰቱመሐከል አንዱ  “ ማዕረረ ትንቢት ማርያም ዘዘመነ ጽጌ እንግዳ ወዘመነ ፍሬ  ጽጋብ  ዘዓመተረኃብ ፍዳ  ብኪ ተአምረ ዘይቤ ኢዩኤል ነቢየ ኤልዳ ያንጸፈጽፍ እምአድባሪሁ ወእምአውግሪሁለይሁዳ  ፀቃውዐ   መዓር  ቅድው  ( ጥዑም ) ወሀሊብ ፀዓዳ ”  በመከር ጊዜ አበባ፣ በአበባ ጊዜደግሞ መከር አዝመራ ማጨድና መሰብሰብ የለም፡፡ ምክንያቱም ጊዜያቸው የተለያየ ስለሆነ፡፡ለምሳሌ በመስከረም ወር የአበባ ጊዜ በመሆኑ አዝመራ መሰብሰብ የለም፡፡ የትንቢት መከርመካተቻ የሆንሽ እንደ ዘመነ ጽጌ የረሃብን ዘመን ያስወገድሽ ማርያም ሆይ፣ የኤልዳ ነቢይ ኢዩኤልከይሁዳ ተራሮች ጣፋጭ ማርና ፀዐዳ ወተት ይፈሳል ብሎ የተናገረው ትንቢት በአንቺ ታወቀ፣ተፈጸመ ፡፡ እመቤታችን ነቢያት የተናገሩት የትንቢት ዘር ተፈጸመባት፡፡ ማለትም ነቢያትየአምላክን ሰው የመሆን ነገር በተለያየ ሁኔታ ተናግረዋል፡፡ ጌታችን ነቢያት የተናገሩት ትንቢትመፈጸሙንና ይህንን ፍጻሜ ለማየት የታደሉት ሐዋርያት መሆናቸውን ‘’አንዱ ይዘራል አንዱምያጭዳል ‘’ የሚለው ቃል እውነት ሆኗል፡፡ እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድሰደድኳችሁ፡፡ ሌሎች ደከሙ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ በማለት ተናግሮአል (ዮሐ.4÷37-38)፡፡

ይህም ነቢያት የዘሩት ትንቢት በሐዋርያት ዘመን ለአጨዳ ለፍሬ መድረሱን መናገሩ ነው፡፡ስለሆነም “ማዕረረ ትንቢት” የትንቢት መካተቻ ማርያም አላት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፍሬክርስቶስን ያስገኘችና ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች እየተባለ የተነገረላት በመሆንዋ ድንግልማርያም  በአበባ ትመሰላለች፡፡ስለዚህ እመቤታችን በመከር ወራት የምትገኝ አበባ ናት፡፡ በመከር ጊዜ የአበባ መገኘት ያልተለመደስለሆነ “ወዘመነ ጽጌ እንግዳ” እንግዳ የሆነ አበባ አላት፡፡

ከዚህ በኋላ ብኪ ተአምረ ዘይቤኢዩኤል ነቢየ ኤልዳ፣ ያንጸፈጽፍ እምአድባሪሁ ወእምአውጋሪሁ ለይሁዳ፣ ፀቃውዓ መዓር ጥዑምወሀሊበ ፀዓዳ” በማለት ነቢዩ ኢዩኤል የተናገረውን ትንቢት አፈጻጸም ይናገራል፡፡ ነቢዩ ኢዩኤልበዘመኑ ጽኑ ረኅብ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን በምሕረት እንደሚጐበኛቸውና ረሃቡእንደሚጠፋ ይነግራቸው ነበር፡፡ “ብዙ መብል ትበላላችሁ÷ ትጠግቡማላችሁ፣ ከዚህ በኋላእንዲህ ይሆናል፣ ተራሮች በተሃ ጠጅ ያንጠበጥባሉ÷ ኮረብቶችም ወተትን ያፈስሳሉ÷ በይሁዳምያሉት ፏፏቴዎች ሁሉ ውኃን ያጐርፋሉ” (ኢዩ 3÷18፣ 2÷26) ።

በዚህ በወርኃ ጽጌ ( በዘመነ ጽጌ )   የሚጾሙ ክርስቲያኖች ሲኖሩ ጾመ ጽጌ መንፈሳውያን ሰዎችሳይታዘዙ በራሳቸው ፈቃድ የሚጾሙት ጾም ነው፡፡ ወይም የትሩፋት ጾም ይባላል፡፡ በቀኖናከታዘዙት ከ7ቱ አጽዋማት ውጪ ትርፍ ጾም ማለት ነው፡፡ ከታዘዘው አትርፎ የጾመ ሰውየመጾሙን ዋጋ ያገኛል፡፡ ብዙ መንፈሳዊ ሥራ የሰራ ሰው ብዙ ክብር እንደሚያገኝ መጽሐፍይናገራል፡፡ “እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ሐጢአትዋ ተሰርዮላታል፡፡ ጥቂት ግን የሚሰረይለትጥቂት ይወዳል’’ (ሉቃ.7፥47) የጽጌን ጾም የሚጾሙ ሰዎች በክብርም ከእመቤታችን ጋርይተባበራሉ፡፡ ነገር ግን የጽጌን ጾም የሚጾሙ ሰዎች ለመመጻደቅ መጾም የለባቸውም፡፡ የማይጾሙሰዎችንም መንቀፍና መክሰስ የለባቸውም፡፡ የጽጌ ጾም እንዲጾም በቀኖና ቤተክርስቲያን ከሰባቱአጽዋማት አንዱ ተደርጎ ስላልተወሰነ የማይጾሙ ሰዎች ሕገ ጾምን እንዳፈረሱ አድርጎ መውሰድስሕተት ነው፡፡ ይልቁንም የሚጾሙ ሰዎች ቢችሉ መጾማቸው እንዳይታወቅባቸው ቢያደርጉየተሻለ ነው፡፡ “ስትጾሙ እንደግብዞች አትጠውልጉ”  (ማቴ. 6፥16 ) ። የተባለው ለዚህ ዓይነቱጾም ነው፡፡

ጽጌ ማለት አበባ ማለት  ሲሆን  ምድሪቱ  በአበባ  የምትሞላበት ጊዜ በመሆኑ አበው ሊቃውንትእመቤታችንን በብዙ ኅብር መስለዋታል፡፡ በአበባ /ጽጌ/፣ በወይን ሐረግ፣መልካሙን የወይን ፍሬአስገኝታለችና አበባ ፍሬን እንዲያስገኝ ድንግል ማርያምም ለሰው ያልተቻለውንና የማይቻለውንአንዴ ብቻ የሆነውን መለኮትን በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት በማህፀንዋ ወሰነችው ፡፡   አዳምናልጆቹ እንዳይበላ በተከለከለችዋ ፍሬ ምክንያት ገነትን ከሚመስል ቦታ እግዚአብሔርን ከሚያክልጌታ ተለዩ የሰው ልጅ ድቀት ተጀመረ ሁሉን አጣ የመጀመሪያ በደል /ጥንተ አብሶ/ ማለት ይህነው፡፡ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር የመለየትን ረጅም ግዜን ገፋ ገዥ የነበረው የሰው ልጅ ተፈጥሮሰለጠነበት፣ ጠላት በዛበት፣ ምድሪቱ ከፋችበት አዳምም ባለቀሰው መሪር እንባ 5500 ዘመንሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሐልሁ የሚል ተስፋ ተሰጠው የህይወት ፍሬንም ዳግምእንዳይበላ በሱራፊ ታጠረችበት፡፡

ያ የጨለማ ዘመን ፍጹም ተስፋ ያልጠፋበት ፍጹምም ተስፋ ያልተፈጸመበት ዘመን ነበር፡፡እግዚአብሔር ከአዳም ጀምሮ ለአርእስተ አበው ቃል ኪዳን ይገባ ነበር፡፡ በዚህም ቃል ኪዳንውስጥ እመቤታችን በተስፋ አበው ውስጥ ታልፍ ነበረ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በድጓ “ማርያምሰተሐቱ ውስተ ከርሱ ለአዳም ከመ ባህርይ ጸአዳ ፤ ማርያምም በአዳም አብራክ ውስጥ እንደ ነጭዕንቁ ታበራ ነበር” በማለት ቅ ገልጦአታል፡፡ ነገር ግን የአበው ተስፋ፣ የነቢያት ትንቢት ሲፈፀምየድንግል ማርያም የህይወት ፍሬ/ በገነት ተከልክላ የነበረችው የገነት ፍሬ/ አማናዊው ጌታ የሚበላየሕይወት ፍሬ ሆኖ ከእመቤታችን ተወለደ ቅዱስ ኤፍሬም በሐሙስ ውዳሴ ማርያም ሲናገር ‘’ከፈለነ ንብላዕ እምዕጸ ሕይወት ዘውዕቱ ሥጋሁ ለክርስቶስ ወደሙ ክቡር በእንተ ፍቅረ ዚአነመጸአ ወአድኅነነ ፤  ዳግመኛ ከዕፀ ኅይወት  እንበላ ዘንድ አደለን ይኸውም እኛን  ስለመውደድሰው ሆኖ ያዳነን የክርስቶስ ክቡር ሥጋው  ክቡር ደሙ ነው ‘’ በማለት እንደገለጸው፡፡  በወርኃጽጌ እመቤታችን ጌታን በጀርባዋ አዝላ በረኀ ለበረሃ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር የተሰደደችበትንሙሉ  ታሪክ  በጥልቀት ስንመለከት ፡፡

 “ልጄን ከግብፅ ጠራሁት”።  /ት.ሆሴዕ 11፥1/ የሚለውን  የትንቢት ቃል የተናገረው ከክርሰቶስ ልደት በፊት በስምንተኛው ምእተ ዓመትአጋማሽ ገደማ የነበረው  የብኤሪ ልጅ ነቢዩ ሆሴዕ  ነው።  ሆሴዕ  ማለት   እግዚአብሔርያድናል ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ታሪኳ ከተዘረዘሩላት ሀገሮች መካከል ግብጽ አንዷስትሆን ግብጽ የብዙኀን አባት አብርሃም በረሃብ ምክንያት የተሰደደባት፣ ዮሴፍ በባርነትየተሸጠባት፣ ወገኖቹ እስራኤላውያን ለሁለት መቶ አስራ አምስት ዓመታት ያህል በባርነትየተገዙባት በኋላም የአለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋርየተሰደደባት ሀገር ስትሆን መሪዎቿም አህዛብ አማልዕክቷም ጣኦታት ነበሩ፡፡ ነቢዩ ሆሴዕየጌታችንን ሥደት ቀድሞ በትንቢት ከተናገሩት ውስጥ  አንዱ ሲሆን ልጄን ከግብፅ ጠራሁትበማለት የስደቱን ማብቃት ተናግሯል፡፡ በዚህ ትንቢት መሰረት መሰደዱን አልተነበየም፡፡ ነገር ግንከስደት መመለሱን መናገሩ ካልተሰደደ መመለስ የለም በመመለሱ መሰደዱን ተናገረ፡፡

የጌታን ሕይወት ከእመቤታችን የእመቤታችንን ከጌታ ለያይቶ ማየት አይቻልም መለኮታዊተግባራትን እና የማዳን ስራዎችን  ካልሆነ በቀር ምክንያቱም ለእርሱ ብቻ የተወሰነና ሊያደርገውየተገባ የአባቱ ተልዕኮ ስለነበረ “ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም አንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግከሰማይ ወርጃለሁ”/ዮሐ.6፥38 ፣ ዮሐ.5፥30/ ። ነቢያት የተነበዩት ጊዜ ደርሶ በነቢዩ በሆሴዕእንዳለውና መልአኩ ገብርኤል ለዮሴፍ ተገልጦ እንደነገረው አንድ ልጇን ይዛ ወደ ግብጹተሰደደች /ማቴ.2፥13/። Continue reading

ጾመ ፍልሰታ፤ የእመቤታችን ዕረፍት፤ ትንሣኤና ዕርገት

ጾመ ፍልሰታ የእመቤታችን ዕረፍት፣ ትንሣኤና ዕርገቷ የሚታሰብበት ወቅት ነው፡፡ እመቤታችን በተለያዩ ጊዜያት ሞትና ትንሣኤዋን ለሐዋርያት የገለጸችበትን ምስጢር ከነሐሴ 1-16 ድረስ ምእመናን በጾም በጸሎት ተወስነው የልጇን ቸርነት የእርሷን አማላጅነት በሱባኤ ይማጸናሉ፡፡ የሱባኤው ወቅት ሲፈጸም “እመቤታችን በእውነት ተነሥታለች” ብለው በደስታ የጾሙን ወቅት ይፈጽማሉ፡፡ ሞቷ የሚያስደንቅ መሆኑን ቅዱስ ያሬድ “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የሐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው፡፡ የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል” በማለት ገልጾታል፡፡

በኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ 64 ዓመታት ያህል ቆይታ አርፋ ተነሥታ በክብር አርጋለች፡፡ ይህንን የትንሣኤና ዕርገት ዐቢይ ምሥጢር ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ተንሥአ እግዚኦ” ውስተ ዕረፍትከ፡፡ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፡፡ አንተና የመቅደስህ ታቦት” /መዝ.131፡8/፤ እንዲሁም “ወትቀውም ንግሥት በየማንከ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት፤ በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” /መዝ.44፡9/ ሲል የተናገረው ቃለ ትንቢት በንጽሐ ሥጋ፣ በንጽሐ ነፍስ፣ በንጽሐ ልቡና የጸናች የቅድስት ድንግል እመቤታችንን ዕረፍት፣ ትንሣኤ፣ ፍለሰት /ዕርገት/ ያስገነዝባል፡፡ /ራእ.11፡19/

እመቤታችን ታቦተ እግዚአብሔር መሆኗን አባ ጽጌ ድንግል በማኅሌተ ጽጌ ሲገልጽ ከመ ታቦት ሥርጉት በወርቀ ዓረብ ወተርሴስ በድንግልና ማርያም ሥርጉተ ሥጋ ወነፍስ ሲል አመስግኗታል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በትርጓሜያቸው ይህንን ቃለ ትንቢት ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ ከገለጣት “ንግሥተ ሰማይ፤ የሰማይ ንግሥት” /ራእ.12፡1/ ጋር በማገናዘብ የእመቤታችንን ሁለንተናዊ ክብርና ልዕልና አምልተውና አስፍተው ገልጸውታል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ “… በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው፡፡….. ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ ሥራቸውም ይከተላቸዋል” /ራእ.14፡13/ ብሎ እንደመሰከረው እመቤታችን ከዕረፍቷና ዕርገቷ በኋላ የመጨረሻ ወደ ሆነው ክብር መሸጋገሯ ያስረዳል፡፡

ይህንን ክብርዋን በመረዳት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር “ወበእንተዝ ናዐብየኪ ኩልነ ኦ እግዝእትነ ወላዲተ አምላክ ንጽሕት ኩሎ ጊዜ፡፡ ንስአል ወናንቀዐዱ ኀቤኪ ከመ ንርከብ ሣህለ በኀበ መፍቀሬ ሰብእ፤ ሁልጊዜ ንጽሕት የምትሆኚ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ ስለዚህ ነገር እናከብርሻለን፣ እናገንሻለን፡፡ ሰውን ከሚወድ ልጅሽ ዘንድ የቅርታንና ምሕረትን እናገኝ ዘንድ ሁል ጊዜ ዓይነ ልቡናችንን ወደ አንቺ እናነሣለን፡፡ በማለት ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያም ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ ሁል ጊዜ ዓይነ ልቡናችንን ወደ አንቺ እናነሣለን፡፡ በማለት ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያም ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣትን ልዩ የቃል ኪዳን ጸጋና አምላካዊ ክብር እያመሰጠሩ ያመሰግኗታል፡፡ ሊቁ “ቀስተ ደመና ማርያም ትእምርተ ኪዳኑ ለኖኅ፣ ዘእግዚአብሔር ሤመኪ ለተዝካረ ምሕረት ወፍትሕ፣ ህየንተ ቀስፍ ለምድር ወአማሰና አይኅ፡፡ ብሎ እንዳመሰገናት፡፡

እመቤታችን በአጸደ ሥጋ ሳለች ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ በተዋሕዶ ሰው ሆኖ በመዋዕለ ሥጋዌ ላደረገው የድኅነት ዓለም ጉዞ ምክንያት ነበረች፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ባርነትና ስደት ለማጥፋት ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ የሰው ልጆችን ያሳደደ ሠይጣን በሄሮድስ አድሮ ሲያሳድደው ልጇን ይዛ በመሰደድ ለድኅነታችን ምክንያት ነበረች፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በራእዩ እንዳየው፤ “ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች፡፡ እርስዋም ፀንሳ ነበር፡፡ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጨንቃ ጮኸች፡፡ ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ፡፡ አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔር ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ፡፡ ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስልሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሀ ሸሸች ”/ራእ.12፡1-6/

 

“ዘንዶውም ወደ ምድር እንደተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት፡፡ ከእባቡም ፊት ርቃ አንድ ዘመን፣ ዘመሃትም፣ የዘመን እኩሌታ ወደምትመገብበት ወደ ሥፍራዋ፣ ወደ በረሀ እንድትበር ለሴቲቱ ሁለት የትላቁ ንሥር ክንፎች ተሰጣት፡፡ እባቡም ሲቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውኃ ከአፉ በስተኋላዋ አፈሰሰ፡፡ ምድሪቱም ሴቱቱን ረዳቻት፡- ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው፡፡ ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ፤ በባሕርም አሸዋ ላይ ቆመ፡፡” /ራእ.12፡13-17/ ሲል መስክሮአል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያውን አምላካዊ ድንቅ ተአምር ባደረገበት በቃና ዘገሊላ ሠርግ ቤት እመቤታችን ከልጇ ከወዳጇ ጋር እንደነበረችና ለተአምሩም ምክንያት ነበረች፡፡ በገሊላ ቃና የተፈጸመው ታላቅና ድንቅ አምላካዊ የቸርነት ሥራ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ የፈጸመውን የቤዛነት ሥራ ሲያደርግ ምክንያት የነበረችው እመቤታችን ነች፡፡ ይኸውም በቀራንዮ አደባባይ በተሰቀለባትና ማየ ሕይወት የሆነውን አማናዊ ወይን ደሙን ባፈሰሰባት ዕለት ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያም ከእግረ መስቀሉ አጠገብ ነበረች፡፡ በዚህም አዲሲቷ ሔዋን እመቤታችን በክርስቶስ ቤዛነት ለዳነውና በወርቀ ደሙም ለተዋጀው አዲሱ የሰው ዘር ማለትም የክርስቶስ ምሥጢራዊ አካል /ቤተ ክርስቲያን/ መንፈሳዊት እናት ሆና በጸጋ ተሰጥታናለች /ዮሐ.19፡26-27/

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሞትና ትንሣኤ ነገረ ማርያም፣ ስንክሳርና ተአምረ ማርያም እንደሚያስረዱት፤ ጥር 21 ቀን ዐርፋለች፡፡ እረፍቷን ቅዱስ ዳዊት ሲናገር “አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” መዝ.136፡8 ፈጣሪዬ ሆይ ምእመናንን ወደምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህን ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ ሲል ቅዱስ ዳዊት ተናግሯል፡፡ ይህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 64 ዓመት በዚህ ዓለም ከኖረች በኋላ ነብሷ ከሥጋዋ ተለይቶ እንደ ልጅዋ ትንሣኤ መነሣቷን የሚያመለክት ነው፡፡ ታቦት ያላትም ማደሪያው ስለሆነች ነው፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን “ወዳጄ ሆይ ተነሺ ውበቴ ሆይ ነይ እነሆ ክረምት አለፈ ዝናቡም አልፎ ሄደ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፡፡ የዜማም ጊዜ ደረሰ የቀረ… ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጐመራ ወይኖችም አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ፡፡ ወዳጄ ሆይ ተነሺ ውበቴ ሆይ ነይ” ሲል ስለ እመቤታችን በምሳሌ ተናግሮአል፡፡ መኃ 2፡1አ-13

ወዳጁን ውበቱን ተነሺ ነይ እያለ የተጣራው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ተጠሪዋም እመቤታችን ናት፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ ማለት በስደት በአይሁድ የዘወትር ጠላትነት በልጅዋ መከራና ስቅላት ስምዖን በቤተ መቅደስ እንደተናገረ ልቧ በሀዘን ሠይፍ የተከፈለበት በሀዘን ፍላጻ የተወጋበት የመከራ ክረምት /ወቅት/ አልፎ የክርስቶስ ሕማሙ ፣ ሞቱ፣ ቤዛነቱ ተፈጽሟል፡፡ ትንሣኤው በምድር ላይ ተገልጧል፣ ተሰብኳል ማለት ነው፡፡ በምድራችን አበባ ታይቷል ማለት የሐዋርያት ድምፅ በምድር ሁሉ ደርሷል ማለት ነው፡፡

ነቢዩ ዳዊት ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ ብሎ ስለ ሐዋርያት የተናገረው በዓለም ያለውን መከራ ስድት ሲገልጽ ነው፡፡ /መዝ 18¸4/ የዜማም ጊዜ ደረሰ ያለው የመከራን ጊዜ ነው፡፡ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ በደስታ ይጮሃሉ፣ ይዘምራሉም ተብሏል፡፡ መዝ 14፡13 የመከር ጊዜ ደረሰ የተባለው መከር የፍሬ ጊዜ በመሆኑ ክርስትና አፍርቷል ማለት ነው፡፡ በለሱ ጐመራ ማለት ደግሞ በጐ ምግባረ ፍሬ ሳያፈሩ የነበሩ ሰዎች በጐ ምግባር መሥራት መጀመራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ በመጨረሻም ወይኖች አብበዋል፣ መዓዛቸውንም ሰጥተዋል እንደተባለ በመላው ዓለም አብያተ ክርስቲያናት በሃይማኖት ማበብ መዓዛ ምግባራቸውን ማቅረብ ከጀመሩ በኋላ እመቤታችን አረፈች፡፡

እመቤታችን ጥር 21 ቀን እረፍት በሆነበት እለት ሐዋርያት የእመቤታችንን ሥጋ ለማሳረፍ ወደ ጌቴሰማኒ መካነ እረፍት ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በቅንዓት መንፈስ ተነሣሥተው “ቀድሞ ልጅዋን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሳ፡፡ በአርባኛው ቀን ወደ ሰማይ አረገ፡፡ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል” እያሉ በማስተማር ሕዝቡን ፈጽመው ወስደውታል፡፡ አሁን ደግሞ ዝም ብለን ብንተዋት እርሷንም እንደ ልጅዋ ተነሣች አረገች እያሉ በማስተማር ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን; ኑ ተሰብሰቡና በእሳት እናቃጥላት ብለው ተማክረው መጥተው ከመካከላቸው ታውፋኒያ የተባለው ጐበዝ አይሁዳዊ ተመርጦ ሄዶ የእመቤታችንን ሥጋ የተሸከሙትን አልጋ ሽንኮር ያዘ፡፡ የአልጋውን ሽንኮር በያዘ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሠይፍ ሁለት እጁን ስለ ቆረጣቸው ከአልጋው ሽንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ ታውፋንያ በፈጸመው ድርጊት ተጸጽቶ ወደ እመቤታችን ስለተማጸነ በተአምር የተቆረጡ እጆቹን እንደ ቀድሞ አድርጋ ፈውሳዋለች (ስንክሳር ዘጥር፡፡)

የእግዚአብሔር መልአክ የእመቤታችን ሥጋ ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ተድላ ደስታ ወደ አለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቁ፡፡ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው፡፡ እነርሱም ትወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት፡፡ ያን ጊዜም ከእፅ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን የማርያም ሥጋዋ ወጣ፡፡ ጌታችንም ዘላለማዊ ወደሆነ መንግሥተ ሰማያት መላእክት እና ሰማእታት እየሰገዱላት አሳረጓት፡፡ ንጉሥ ዳዊት “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋ ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” እንዳለ፡፡ መዝ 44፡9

ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ተመልሶ ከሰማይ ወረደ፡፡ ሐዋርያት ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው፡፡ እርሱም እንዳየ እንደሰማ ሥጋዋም በታላቅ ክብር ማረጉን ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ፡፡ የነሐሴም ወር በባተ /በገባ/ ቀን ዮሐንስ እንዲህ አላቸው፡፡ የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት ኑ፤ ሁለት ሱባኤ በመጾም እንለምን አለ፡፡ በጾም በጸሎት ሱባኤ ያዙ፤ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ አምጥቶ ስለሰጣቸው በታላቅ ዝማሬ፣ በውዳሴና በምሕላ ወስደው ቀድሞ በተዘጋጀው መካነ እረፍት በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡ Continue reading

የብፁዕ አቡነ እንድርያስ መታሰቢያ የአብነት ት/ቤትና ሙዚየም በገረገራ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን

መቂት በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ከአዲስ አበባ 740 ኪሎ ሜትር ምትገኝ ከተማ ናት፡፡ የመቂት ከተማን እንድመለከት ምክንያት የሆነኝ የብፁዕ አቡነ አንድርያስ 23ኛ ዓመት በዓለ እረፍት ለማሰብ የዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት የመንፈስ ልጆቻቸው በትውልድ ሀገራቸው ለመታሰቢያ እንዲሆናቸው የታሰበውን የአብነት ት/ቤትና ሙዜየም የመሠረት ድንጋይ ለማስቀመጥ ከተመደቡት የመንበረ መንግሥት (ግቢ) ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት አባላት ባደረኩት መንፈሳዊ ጉዞ ነው፡፡

ለመቂት ከተማ ግርማ ሞገስ የሆነው የገረገራ ደብረ ሃይማኖት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጠንቅቀው የሚያውቁ ስመ ጥር ሊቃውን የወጡበት አንጋፋና ጥንታዊ ደብር ነው፡፡ ገረገራ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ካፈራቻቸው ሊቃውንት መካከል መምህር ደስታ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተሾሙ አራት ጳጳሳት አንዱ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ መምህር መንግሥቱ ውሂብ፣ መምህር ቀፀላ ሰይፈሥላሴ እና ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ቀዳማዊ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ባለውለታ የነበሩ ሊቃውንት ማሰብ እንደሚገባን ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይመክረናል፡፡ “የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው” /ዕብ 13፥7/ እንዲል፡፡

የብፁዕ አቡነ እንድርያስ ፍሬ የዓምደ ሃይማኖት ሰ/ት/ቤት

የብዙ ክርስቲያኖች ሕይወት እንዲለወጥ ምክንያት የሆነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የሚገኘውን ሰንበት ትምህርት ቤት በእግዚአብሔር ፈቃድ በወቅቱ የነበረውን የካህናትን እና የምእመናንን አሉታዊ ተጽዕኖ ሁሉ ተቋቁመው የያኔውን ወጣቶች ልብ የእግዚአብሔርን ቃል በመመገብ ˝ዓምደ ሃይማኖት መንፈሳዊ ማኅበር˝ ብለው በ1957 ዓ.ም. መሥረተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ እንድርያስ የዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት ለማቋቋም ወጣቶችን ሲያሰባስቡ ከፍተኛ ፈተና ደርሶባቸው ነበር፡፡ “ወጣቱን ሁሉ እየሰበሰቡ መቅደሱን ሊያረክሱት ነው!” እንዲሁም “ሴቶቹን እየሰበሰቡ ቤተ መቅደስ አስገብተው ቀዳሽ ሊያደርጓቸው ነው!” በማለት በአንዳንድ ሽማግሌዎችና ካህናት ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባቸው ነበር፡፡ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ግን የቤተክርስቲያንን ዓላማ በመግለጽ በጽናት አስተምረዋል፡፡ የተቃወሟቸው ሰዎች ጥረታቸው እንዳይሳካ አብነት ሆነዋል፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ብዙ ልጆች ዕለት ዕለት ወደ ቤተ ክርስቲያን በመምጣት በአገልግሎት ይተጉ ጀመር፡፡

በዚህ መልኩ ወጣቱን ወደ ቤተ ክርስቲያን በማቅረብና የቤተ ክርስቲያን የነገ አለኝታ እንዲሆን ካላቸው ከፍተኛ የሆነ  ፍላጎት የተነሣ ከወጣቱ ጋር በሰንበት ት/ቤት መርሐ ግብር ላይ ሳይታክቱ በመገኘት አብረው ተቀምጠው በመምከርና አቅጣጫ በማስያዝ ጉልህ ሚና ነበራቸው፡፡ ጥያቄ እንኳን ሲጠየቅ ወጣቶቹ በቅድሚያ መልስ እንዲሰጡ ነው የሚፈልጉት፡፡ “እናንተ እርስ በርሳቸሁ ተፋጩ፣ ቢላዋ እርስ በርሱ ሲሳሳል ነው ስለት የሚወጣው” ይላሉ፡፡ በዚህም አባታችን ወጣቶቹ እንዲያውቁ ስለሆነ የሚፈልጉት ማንኛውም መልስ ያለ ፍርሐት እንዲናገሩ ያደርጋሉ፡፡ በመጨረሻም የጠመመውን አቃንተው፣ የጎደለውን አሟልተው፣ አርመውና አስተካክለው ተገቢውን ትምህርት ያስተላልፋሉ፡፡

ዓምደ ሃይማኖት መንፈሳዊ ማኅበር ሲነሣ ሁልጊዜ ከአባላቱ የልቦና ሰሌዳ የማይጠፉ፤ ምክራቸው፣ ተግሣጻቸውና እውነተኛ አባትነታቸው የማይረሳው ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ከሰ/ት/ቤቱ ጉባኤ ዘወትር የማይለዩ ቢታመሙ፣ ተቀይረው ወደ ሌላ ሀገር ስብከት ቢሔዱ ሰንበት ት/ቤቱን ከማሰብ የማይታክቱ ቅንና የማይረሱ አባት ነበሩ፡፡

የአደራ ቃል

ብፁዕነታችን ከማረፋቸው በፊት ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት አስመልክቶ የተናገሩት የአደራ ቃል “ዓምደ ሃይማኖትን እወዳታለሁ፣ ዓምደ ሃይማኖት የተወለድኩባት፣ ያደኩባት፣ የተማርኩባት፣ ምርጫዬ የተደረገባት እንደ ሀገሬ እንደ ገረገራ ናት፡፡ ዓምደ ሃይማኖት በምትመሠረትበት ወቅት ሌሎች ማኅበራት በየቤተክርስቲያኑ የሚቋቋሙበት ወቅት ነበር ስምም አውጥተው ከፓትርያርኩ ዘንድ ሊያፀድቁ ሲያቀርቡ ተቀይሮባቸዋል፡፡ የእርሷ ግን ‘ስምን መልአክ ያወጣዋል እንዲሉ ለዓምደ ሃይማኖት ጋሻ ጃግሬዋ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ነውና መጀመሪያ የወጣላት ስም በፓትርያርኩ ትእዛዝ እንዲጸናላት ተደረገ፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነት ልጆቿ ልጆቼ እንደመሆናቸው መጠን በጸሎት አልለያቸውም፡፡ እወዳቸዋለሁ፡፡ እርሷንም ዓምደ ሃይማኖትን አልረሳትም ጎንደር በነበርኩበት ጊዜ ዓመታዊ በዓሏ እንኳ ሲደርስ በዓሏን ስሟን በጸሎት በማሰብ አከብረው ነበር፡፡ የመታሰቢያዋ ዕለት ለአምላኳ ለአምላኬ ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና የማቀርብበት ነበር፡፡ ዛሬም በሕመም ብቀርም በሐሳቤና በመንፈሴ አብሬያት ሆኜ ወደ ፈጣሪዬ በጸሎት አመለክታለሁ፡፡ ልጆቼን የማበረታታችሁ ልጆቼ ናቸሁና መንፈሳዊነትን ተላብሳችሁ ቅን ሆናችሁ የቀናውን መንገድ ምረጡ፡፡ ልጆቼ የሚሻለኝ ከሆነ እመጣለሁና ቀደም ብላችሁ ዓርብ ዕለት መስከረም 27 ቀን ኑና አስታውሱኝ፡፡ በተረፈ ለምናፍቃት ዓምደ ሃይማኖት ቀሲስ ጌታቸው ደጀኔና ዲያቆን ኃይለ ገብርኤል ይትባረክ (እርሳቸው ሰንበት ት/ቤቱን ሲመሠርቱ አብረዋችው የነበሩ መሥራች አባላትና የመንፈስ ልጆቻቸው) እንደእኔ ሆነው ይናገሩላት፡፡ መታሰቢያሽን የተቀደሰ በዓልሽን በዓለ ሰላም ያድርግልሽ፤ ልጆችሽንም ይባርክልሽ፤ በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን በመንፈሳዊ መበረታታት በትኅትና ያቆይሽ”

 

ዜና ዕረፍት

ብፁዕ አቡነ እንድርያስ በ1987 ዓ.ም የታዕካነገሥት በዓታ ለማርያምና የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል አብያተ ክርስቲያናት የበላይ ኃላፊ በመሆን በመሥራት ላይ እንዳሉ ሞት ለሰው ልጆች የተዋረድ ድርሻ በመሆኑ ባለብዙ ታሪክና የመልካም ሥራ ባለቤት የሆኑት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ከቆዩ በኋላ ሐምሌ 27 ቀን 1987 ዓ.ም በተወለዱበት በመድኃኔዓለም ዕለት በ81 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ዕለተ ሞታቸውን አስቀድመው ያውቁ የነበሩት ብፁዕነታቸው አሟሟታቸው ዕፁብ ድንቅ የሚያሰኝ ነው፡፡ ሐምሌ 27 ቀን 1987 ዓ.ም እርሳቸው ጋር መጥተው ለነበሩት ለብፁዕ አቡነ ዮሴፍ እና ለብፁዕ አቡነ ገብርኤል በፍልሰታ ማርያም የሚካሔደውን የውዳሴ ማርያምንና ቅዳሴ ማርያም ትርጉም ሲያካሔዱላቸው ከቆዩ በኋላ “በሉ ከነሐሴ አንድ ጀምራችሁ እንድታካሔዱት” በማለት ስድስት ሰዓት ሲሆን “የምሳ ሰዓት ደረሰ” ብለው ተናገሩ፤ አስከትለውም እኔም ትንሽ ልረፍ ብለው ተሰነባበቱ፡፡ ከመተኛታቸውም በፊት በተደጋጋሚ ዛሬ ቀኑ ስንት ነው? ስንት ሰዓት ሆነ? እያሉ ይጠይቁ ነበር፡፡ አንድ ኩባያ ወተት ጠጥተው ትንሽ ፋታ እንደወሰዱ፤ ከዚህ አካባቢ እንዳትርቁ በማለት አብረዋቸው የነበሩትን ቤተሰባቸውን እንዲያስተካክሉዋቸው አደረጉ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ሰዓቱ ዐሥር ሲሆን ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለየች፡፡

ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ በመልካም ጤንነት ላይ ሳሉ ሐምሌ 20 ቀን 1987 ዓ.ም ያሳደጉትን ቀሲስ ፋንታሁን ቀፀላን ወደ ትውልድ ሀገራቸው ገረገራ በመላክ የቀብራቸው ሁኔታ እንዲሰናዳ አድርገዋል፡፡ መቃብራቸውም ሐምሌ 27 ከቀኑ በ10፡00 ተሰናድቶ አልቆ ነበር፡፡

የብፁዕነታቸው አስከሬን ወደ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተክርስቲያን ተወስዶ ሐምሌ 27 እና 28 በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የገዳማት አበምኔቶችና የታላላቅ አድባራት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና አያሌ ካህናት በተገኙበት ጸሎተ ፍትሐት ተደርጎላቸዋል፡፡

በወቅቱም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ የብፁዕነታቸውን ታላቅ ሐዋርያነትና አባትነት በመግለጽ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እንደ እርሳቸው ያለ ታላቅ አባት በማጣቷ ጉዳት የደረሰባት መሆኑን አውስተው እንደ እርሳቸው ያለ አባት እንዲተካላት የምትጸልይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከዚያም በሕይወት ዘመናቸው በሰጡት ኑዛዜ መሠረት አስከሬናቸው ተወልደው ወደ አደጉበት ተምረው ወደ አስተማሩበትና ወደ አስተዳደሩበት በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት መቄት ወረዳ ገረገራ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተሸኝቷል፡፡

በመጨረሻም የብፁዕነታቸው አስከሬን የመጨረሻ ማረፊያ በሆነው በገረገራ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ደርሶ በሕይወት ዘመናቸው በሰጡት ኑዛዜ መሠረት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአካባቢው አድባራት አለቆችና የገዳማት አበምኔቶች፣ የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ተወካዮች የሚወዱትና የሚወዳቸው የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን እንዲሁም መላው ቤተሰባቸው በተገኙበት ሐምሌ 30 ቀን 1987 ዓ.ም በሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ መታሰቢያ ዕለት በቤተመቅደሱ በክብር አርፏል፡፡

ውለታ አለመርሳት

የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት የብፁዕ አቡነ እንድርያስ ውለታ ላለመርሳት የብፁዕነታቸው 10ኛ ዓመት በዓለ ዕረፍት መታሰቢያ ሲከበር ሐምሌ 27 ቀን 1997 ዓ.ም. የሕፃናት ክፍልን መጠሪያ በስማቸው ተክለ እንድርያስ በማለት ሰይሟል፡፡

በየዓመቱ የብፁዕ አባታችን በዓለ ዕረፍት በሰንበት ት/ቤቱ አዳራሽ ማክበር በቂ እንዳልሆነ ያመኑበት በሰሜን አሜሪካ፣ በካናዳ፣ በአውሮፓና በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ የዓምደ ሃይማኖት አባላት እኛ በሕይወት እያለን እሳቸውንም የሚያውቁ አባቶች ከማለፋቸው በፊት በትውልድ ቦታቸው የአብነት ት/ቤትና ሙዜየም እንዲሠራላቸው ሀሳብ አፈለቁ፡

የተቀደሰውን ሀሳብ እውን ለማድረግ በሕይወት እያሉ ጉባኤ ዘርግተው በሚያስተምሩበት በገረገራ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የመስቀል ቅርጽ ያለው የንባብ ቤት፣ የቅዳሴ ቤት፣ የቅኔ ቤት፣ የትርጓሜ ቤት፤ የአብነት ት/ቤትና ሙዜየም ለማሠራት አሁን ባለው የዋጋ ጥናት ብር 4,750,000.00 /አራት ሚሊዮን ሰባት መቶ አምሳ ሺሕ/ ብር በ3,200 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ መንፈሳዊ ት/ቤት ለመገንባት ሐምሌ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ በብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ላሊበላ ገዳም የበላይ ጠባቂ የመሠረት ድንጋይ ተጣለ፡፡ ቅየሳ ተካሔደ፤ ቁፋሮ ተጀመረ፡፡

የመሠረት ድንጋይ በተጣለበት ዕለት ከዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት የሔዱ አራት ታዳጊ ሕፃናት ግብረ ዲቁና ከብፁዕ አቡነ ኤርምያስ አንብሮተ ዕድ ተቀበሉ፡፡ ግንባታውን ጀምሮ ለማጠናቀቅ የሚፈለገው ገንዘብ በወቅቱ ከተገኘ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይገመታል፡፡ Continue reading