የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 23 ሙሉውን ስንመለከት ጸሐፍት ፈሪሳውያን በስፋትና በተገቢ የተወቀሱበት ክፍል ሆኖ እናገኘዋለን፤ ወቃሹም ደግሞ ሁሉን የሚመረምር፣ ማን ምን እንደሆነ የሚያውቅ፣ እንደሰዎች፣ በሰዎች ንግግር የማሳመር ችሎታ የማይታለልና ልብና ኩላሊታችንን መርምሮ የሚያውቅ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
ጸሐፍት ፈሪሳውያን እዩን እዩን የሚሉ ግብዞች፣ በጸሎት አሳበው የመበለቶችን ቤት የሚበሉ፣ እውነተኞችን የሚያሳድዱ፣ በሙሴ ወንበር ላይ ተቀምጠው ትክክለኛውን ነገር ለማስመሰል የሚናገሩ ግን ደግሞ በፍጹም የማያደርጉት ናቸው፡፡ እነዚህ ጠባያትና ግብሮቻቸው ናቸው በፈጣሪያቸው እንዲወቀሱ ያደረጋቸው፡፡ በተለይ ተቀባይነት እንዲያገኙ በእርሱ ስምና በቃሉ እንዲሁም በሚለብሱት የአገልግሎት ልብስ ላያቸውን ያሳመሩ ውስጣቸው ግን ርኩሰትን የተሞሉ መሆናቸውን ሲገልጽ፡- “እናንት ግብዞች ጸሐፊዎችና ፈሪሳውያን፣ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን ዐጥንት፣ ርኩሰትም ሁሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ ወዮላችሁ፡፡” ይላቸዋል፡፡ /ማቴ 23፥27/ ከዚህ የምንረዳው ጌታችን ያወገዛቸው ብቻ ሳይሆን በዚህ ተግባራቸው ወደፊት የሚገጥማቸው ነገር አስፈሪ መሆኑን ነው፡፡ በዚሁ ምዕራፍ ላይ ቁጥር 13 እና ቁጥር 15ን በቅደም ተከተል ስናይ መንግሥተሰማያት ስለማይገቡና ስለማያስገቡ፣ ምእመናንን ከእነሱ ይልቅ ሁለት እጅ እጥፍ የገሃነም ልጆች ስለሚያደርጉና በጸሎት እያመካኙ የመበለቶችን ቤት ስለሚበሉ “ወዮላችሁ!” በማለት ስላደረጉት የሚጠብቃቸውን ቅጣት አመልክቷቸዋል፡፡ በቁጥር 14 ላይም “የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ፡፡” ይላቸዋል፡፡
በዚሁ የመጸሐፍ ቅዱስ ክፍል ከቁጥር 1 ጀምረን ስናነብ እንደምናገኘው፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጸሐፍት ፈሪሳውያንን ጉዳይ ሲነግር የነበረው ለሕዝቡና ለደቀመዛሙርቱ ነበር፡፡ “በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለሕዝቡና ለደቀመዛሙርቱ እንዲህ ብሎ ነገራቸው፡-ጸሐፊዎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል፡፡ ስለዚህ ያዘዟችሁን ሁሉ አድርጉ፣ ጠብቁትም፤ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደሥራቸው አታድርጉ፡፡” /ማቴ 23፥1-3/ ያኔ በዚያን ጊዜ የተናገረው፣ ዛሬ በዚህን ጊዜም እንደሚሠራ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ዛሬም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ ስለ ጸሐፍት ፈሪሳውያን መለያ ጠባያት መግለጹና እነሱን ማውገዙ ብሎም ወደፊት እየጠበቃቸው ስላለው መከራ መናገሩ በየዘመኑ ለሚነሡ ውሉደ ጸሐፍት ፈሪሳውያንም አጥብቆ ያገለግላል፡፡ በዘመናችን የጸሐፍት ፈሪሳውያንን ጠባያት የያዙ የሉምን? በርካቶች አሉ፡፡ ጌታችን እንደገለጻቸው በግብዝነት፣ በአስመሳይነትና በንዋይ ወዳድነታቸው የተዋጣላቸው ሲሆን፣ በተለይም በቃሉ እያታለሉ የሚሠሩት ያልተገባ ተግባር፣ ምንም እንኳን ውስጣቸው ባዶ ሆኖ ዛሬ ሁሉ የሞላላቸው ቢመስሉም፣ በእውነት ለንስሐ የተሰጣቸው ጊዜ ሲጠናቅ ፍጻሜያቸውን አለማሰብ ነው፡፡
ከላይ በርዕሱ ላይ እንደተመለከተው “እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደሥራቸው አታድርጉ” /ማቴ 23፥3/ ተብሎ እንደተነገረን፣ ዛሬ ጹሙ የሚሉ ግን በተገቢው ሁኔታ የማይጾሙ፣ ጸልዩ የሚሉ ግን የማይጸልዩ፣ ስለምጽዋት ሲናገሩ የተመሰገኑ ግን የማይመጸውቱና መጽውቱ የሚሉትም ለቤተ እግዚአብሔር ሳይሆን ለኪሳቸው የሆነ፣ በሃይማኖት ጽኑ የሚሉ ግን ደግሞ እዛኛውም ቤት እያገለገሉ ደመወዝ የሚበሉ፣ መማለጃን መቀበል የገሃነም ልጅ ያደርጋል የሚሉ ግን እነርሱ በእጥፍ የገሃንም ልጆች የሆኑ በርካቶች አሉ፡፡ ጌታችን እንዳዘዘን፣ መጽውቱ ሲሉን መመጽወት ነው፤ አለመመጽወታቸውንና እጃቸውን ወደ እግዚአብሔር ገንዘብ ሲሰዱ ግን እንከላከላቸው ይሆናል እንጂ እጃችንን እንደእጃቸው ልናደርግ አይገባም፤ አንከተልምም፤ጹሙ ሲሉን መጾም ነው፤ አለመጾማቸውን አናይም ወይም በጠዋት ቡና መጠጣታቸውን አንከተልም፤ አታመንዝሩም ይሉናል፤ መልካም ነው፤ ይህን መልካም ምክር እንከተላለን፤ ጌታችን እንዳዘዘን፣ ሲያመነዝሩና ሲዳሩ አንከተላቸውም፤ በዚህም የነገሩንን እንጂ የሚያደርጉትን አንከተልምና በኃጢአታቸው የሚመጣባቸውን ጣጣም አንቀበልም፡፡
ጌታችን በሥጋዌው ወራት በዚህ ምድር ሲመላለስ በነበረበት ጊዜ የነበሩት ጸሐፍት ፈሪሳውያን መልካም የሚናገሩና የሚናገሩትን ግን የማያደርጉ ነበሩ፡፡ ይህ ተግባራቸው ከግብዝነታቸው፣ ከገንዘብ ወዳድነታቸውና በቃሉ ከመነገዳቸው ጋር የሚያስከትልባቸውን ቅጣት ጌታችን “ወዮላቸው!” ሲል ገልጾታል፡፡ ዛሬ እንዲህ አይነቶቹ ጸሐፍት በብዙ መገኘታቸውና በየቦታው የሚሠሩት የክፋት ሥራ እጅግ የሚደንቅ ሲሆን፣ ከዚህ በላይ የሚያስደንቀው ደግሞ በንግግርም በተግባርም የሌሉበት መሰሎቻቸው መፈልፈላቸው ነው፡፡ እርግጥ ነው ጥሩውን እየተናገሩ አለማድረግም ሆነ ክፋትንና ሰውን ሚያሳስቱ ነገሮችን እየተናገሩ መልካሙን አለመናገርና አለማድረግ አንድ ቢሆኑም፣ መልካም ተናጋሪዎች ግን ደግሞ የተናገሩትን የማይፈጽሙጹ ወዮላቸው ከተባሉ ክፉ ተናጋሪዎችና ክፉ አድራጊዎች ምን ይባሉ ይሆን? የሚናገሩት መልካም፣ የሚተገብሩት ግን ሌላ የሆኑትን ጌታችን እንዳደረገው በየወቅቱ ባለመገሰፃችንና ባለማረማችን ምናልባትም ማውገዝ ሲገባን ባለማውገዛችን ቁጥራቸውን ከመጨመራችን በላይ ከነርሱ የከፉና ንግግራቸው ጭምር መልካም ያልሆነ ከሃይማኖት ወደ ጥርጥር ብሎም ወደ ክህደት የሚወስዱ ከምግባርም የሚያስወጡትን አፍርተናል፡፡ ዛሬ ግን ከጌታችን እንደተማርነው፣ መልካሙን እየተናገሩ ክፉ ሚያደርጉትንም ሆነ፣ ሰውን ማፈር፣ እግዚአብሔርን መፍራት የሌላቸውን ያለምንም ፍርሃት ልንቃወማቸው፣ ልናርማቸው ብሎም ተገቢውን መረጃ ይዘን ልናጋልጣቸው ይገባል፡፡ እስከመቼ እንታገሳቸዋለን? እንደእውነቱ ከሆነ ለእነርሱም የሚሻላቸው ባንታገሳቸው ሲሆን፣ የእኛ ትእግስት (ምናልባትም በትእግስት ስም ፍራቻ ይዞን ይሆናል) የተሰጣቸውን የንስሐ ጊዜ በከንቱ እንዲያሳልፉና የእግዚአብሔርን ቸርነት እንዲሳለቁበት እያደረገ በመሆኑ ለምን ዝም እንዳልናቸው ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል፡፡ እነዚህ ወገኖች እያሳዩ ባሉት አስመሳይነት፣ ሙሰኝነትና ሌላም ሌላም ፈሪሳዊ ጠባያት የሚያገኛቸው ቅጣት “የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ” /ማቴ 23፥14/ በሚል በጌታችን የተነገረ መሆኑን ስናነብ የወደፊቱ የባሰ ይሆናል እንጂ አሁን እየተቀጡ አይደለም ማለት አይደለም፡፡ ዛሬ በአገልግሎት ልብስና በማይተገብሩት የእግዚአብሔር ቃል ተከልለው፣ ከገንዘብ ወዳድነት የራቁ በመምሰል ቤተክርስቲያንን የሚዘርፉ፣ ሃይማኖተኞች መስለው በዐውደ-ምሕረቱና እስከመቅደሱም ዘልቀው ሃይማኖትን ለማጥፋት የተሰገሰጉ ሁሉ እየተቀጡ መሆኑን ከማንም በላይ ራሳቸው ያውቁታል፡፡ እነዚህ ዕድለኞች ሆነው የንስሐ ጊዜ ያገኙ አስመሳዮች ከሕሊና ቅጣት ባሻገር በደዌ ሥጋ ጭምር እየተጠቀጡ ነው፤ በቤተሰቦቻቸው ላይ ጭምር መቅሰፍት እየተቀበሉ ነው፤ አትዝረፉ፣ መማለጃ አትቀበሉ እያሉ በንግግር የሚጠብቁት፣ በተግባር ግን የሚዘርፉት የቤተክርስቲያን ገንዘብ አዕምሯቸውን እንዲስቱ እያደረጋቸውና መጥፊያቸው እየሆነ ነው፤ ከዛሬ ነገ ተነቃብኝ እያሉ የሚኖሩት ቃየናዊ ሕይወትም እያሰቃያቸው ይገኛል፡፡ ይህ እየሆነባቸው ነው እንግዲህ ጌታችን “የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ” የሚላቸው፡፡ ከዚህ የከፋው ፍርድ እንዴት አስደንጋጭና አስፈሪ ይሆን? ሊያውም በፍጡር ሳይሆን በፈጣሪ የተነገረ! አዎ ንስሐ የማይገቡ፣ መሐሪው አምላካችን ብዙ ዝም ሲል ቸርነቱ ላይ የሚያላግጡትን ከዚህ የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ ማለቱ ካልተመለሱ ገና በስጋቸው ብዙ እንደሚቀጡና በተለይም ደግሞ በነፍሳቸው የሚጠብቃቸውን ሲያሳያቸው ነው፡፡ Continue reading